በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር የጎንደር ዩኒቨርሲቲን ጎበኙ
በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር የተከበሩ አምባሳደር ሚካኤል ራይኖር ጥር 11/2010 ዓ.ም ጎንደር ዩኒቨርሲቲን ጎበኙ፡፡
እንደሚታወቀው ጥር 11 ለኢትዮጽያውያን ልዩ ቀን ናት፡፡ በተለይም ለታሪክና የባህል አምባ ለሆነችው ጥንታዊቷ ጎንደር፣ በዚህ ቀን ልዩ ልዩ የባህልና የእምነት ትይንቶች በሚያምር ሁኔታ የሚያሸበርቅበት ዕለት ነው፡፡
[widgetkit id=8138]
ትይንቱንም ለመታደም ከባህር ማዶና ከሀገር ውስጥ ብዛት ያላቸው የበዓሉ ታዳሚዎች በየዓመቱ ወደ መዲናችን ጎንደር ሲተሙ ይስተዋላሉ፡፡ በተለይም በዚህ ዓመት/ በ2010 ዓ.ም የተከበረው የጥምቀት በዓል በዓለም የቅርስ መዝገብ በUNESCO ለማስመዝገብ ሰፊ እንቅስቃሴዎች የተደረጉበት መሆኑን መዘገባችን ይታወቃል፡፡
ታዲያ ይህንን በዓል ለመታደም ከመጡ እንግዶች ለአብነት ያህል መኖሪያቸውን አዲስ አበባ ነገር ግን የባህር ማዶ ዜግነት ካላቸው ጎብኝዎች መካከል የዩናይትድ ስቴትስ -ኢትዮ አምባሳደር የተከበሩ ሚካኤል ራይኖር ይገኙበታል፡፡
44ቱ ታቦተ ህጎች ባህረ ጥምቀት ከተጠናቀቀ በኋላ አምባሳደሩ በዩኒቨርሲቲው የተደረገላቸውን የጉብኝት ግብዣ በመቀበል ዩኒቨርሲቲውን ጎበኝተዋል፡፡፣ ከጉብኝቱ መካከል ቀዳሚው አምባሳደሩ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻን ጨምሮ ከሌሎች የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ጋር ያደረጉት ውይይት ነበር፡፡
በውይይቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ ስለዩኒቨርሲቲው ጠቅለል ያለ መረጃ ካቀረቡ በኋላ ፤ በአሜሪካ ሀገር ከሚገኙ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች ተቋማት ጋር በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በምርምርና በሌሎች ዘርፎች አብሮ የመስራትና የመደጋገፍ ግንኙነቶች ከረዥም ዓመታት ጀምሮ መጀመሩን አውስተው ፣ ለወደፊትም ያሉት ግንኙነቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያላቸውን ሙሉ እምነት ገልጸዋል፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ በግንባታም በኩል የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አዲሱ ተከታታይ ህክምና ክፍል ሙሉ በሙሉ በዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍ መገንባቱን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡
አምባሳደር ሚካኤል በበኩላቸው፣ ከዩኒቨርሲቲው ጋር አብሮ ለመስራትና ለመደጋገፍ የተጀመሩ ስምምነቶች በይበልጥ መጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ አምባሳደሩ በጤና በትምህርትና በመሳሰሉት መስኮች ከዩኒቨርሲቲው ጋር አብረው ለመስራት ያለው እንቅስቃሴ ይበልጥ ጎልብቶ እንዲቀጥል ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ሌሎች አመራሮች የተጀመሩትን ስምምነቶችና ግንኙነቶች ይበልጥ ለማጠናከር ይበጃል ያሏቸውን ሀሳቦችና ጥቆማዎች ለአምባሳደሩ አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም አምባሳደሩ የዩኒቨርሲቲውን ግቢዎች፣ የምርምርና የላቭራቶሪ ማእከላትን እንዲጎበኙ ተደርጎ የጉብኝት ፕሮግራሙ ተጠናቋል ፡፡
ዘጋቢ አምሳሉ ግዛቸው
ኤዲተር ደምሴ ደስታ