በኢፌድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚመራ የልዑካን ቡድን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታልን ጎበኘ፡፡
የፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስራ ዘጠነኛውን ዓመታዊ ጉባዔ “የተሻለ የጤና ስርዓት አፈጻጸም ለሁሉም አቀፍ የጤና አገልግሎት ሽፋን መሰረት ነው” በሚል መሪ ቃል በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በጎንደር ከተማ ከጥቅምት 29 እስከ ህዳር 1/2010 ዓ.ም አካሂዷል፡፡ ጉባዔው የፌደራልና የክልል መንግስታዊ አካላት፣ የክልል የጤና ቢሮ አመራሮች፣ የሆስፒታል ስራ አስኪያጆች እና የዘርፉ አጋር አካላትን ያሳተፈ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በጉባዔው መርሀ ግብር መሰረት የልዑካን ቡድኑ ጥቅምት 28/2010 ዓ.ም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ያለውን አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል፡፡
[widgetkit id=7225]
በዕለቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል 1928 ዓ.ም ጀምሮ በጎንደርና አካባቢው ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍል የጤና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አውስተው፣ ያሁኑ የጎንደር የኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ 1947 ዓ.ም የማህበረሰብ ጤና አጠባበቅ ኮሌጅ በመሆን ከተመሰረተ ጀምሮ ለሀገሪቱ ብሎም ለሌሎች የዓለም ክፍሎች ብቁ የጤና ሙያተኞችን በማፍራት በሀገራችን የሚገኝ ግንባር ቀደም ተቋም መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር አኒሳ በፈቃዱ ስለ ሆስፒታሉ ታሪክ እና አጠቃላይ ገፅታ ለእንግዶች አጠር ያለ ማብራሪያና ገለጻ ካደረጉ በኋላ የተቋማቸውን አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ አስጎብኝተዋል፡፡ የሆስፒታሉ የመሰረተ ልማት ግንባታ የሚገኝበት ሁኔታ፣ የላቦራቶሪዎች የስራ ላይ ትግበራ፣ የኩላሊት እጥበት ማዕከል፣ የካንሰር ህክምና ማዕከል እና ሌሎችም በእንግዶቹ ከተጎበኙት ውስጥ ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የልዑካን ቡድን እና የጉባኤው ተሳታፊዎች በጉብኝቱ ወቅት በተመለከቱት በሆስፒታሉ እየተካሄደ ባለው የስራ እንቅስቃሴ እና የማስፋፊያ ግንባታ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
በአምሳሉ ግዛቸው
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙት ዳይሬክቶሬት

