በጎንደር ዩኒቨርሰቲ ሁለት ዶክተሮች በዩሮ ጋይናኮሎጂ በፔልቪክ ፍሎር ሪኮንስትራክቲቭ ሰርጀሪ በስፔሻሊቲ ሰርትፊኬት ተመረቁ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በማህፀንና ፅንስ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶ/ር ብርሃኑ አበራና ዶ/ር ዘላለም መንግስቱ በዩሮ ጋይናኮሎጂና በማህፀን ግድግዳ ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ጥገና (Pelvis floor reconstructive surgery) በሰብ ስፔሻሊቲ ለሁለት ዓመታት ከጀርመን አገር በመጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ትምህርቱን ሲከታተሉ ቆይተው ጥር 17/2010 ዓ.ም በሰርተፍኬት ተመርቀዋል፡፡ በጀርመን ሀገር የማህፀንና ፅንስ ህክምና ዶ/ር የሆኑት ዶ/ር አና ኪፈር (Anna Kiefer) እና በጀርመን የዩሮ ጋይናኮሎጂና የፔልቪክ ፍሎር ሪኮንስተራክሽን ማህበር ፕሬዚዳንት (President of Urogynecology and Pelvis floor reconstructive surgery association) የሆኑት ፕ/ር ገርት ናውማን (Gert Naumann) እንዲሁም የዶ/ር አና ባለቤት የሆኑት ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ደብሩ አዲሳ፤ ስልጠናውን በተከታታይ ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህፀንና ፅንስ ትምህርት ክፍል እየተመላለሱ በመስጠትና በመጨረሻም ሰልጣኞች በውጪ ፈታኞች እንዲፈተኑ በማድረግ በዚህ የሙያ ዘርፍ በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆኑት ዶ/ር ብርሃኑ አበራና ዶ/ር ዘላለም መንግስቱ ለምረቃ በቅተዋል፡፡
[widgetkit id=8152]
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በህክምና ዶክትሬት ዲግሪ የተመረቁትና በዘርፉ በሀገር ውስጥና በውጪ ሃገር ከፍተኛ ዕውቀት ያካበቱት የዶ/ር አና ባለቤት የሆኑት ዶ/ር ደብሩ አዲሳ በወቅቱ እንደገለፁልን ዩሮ ጋይናኮሎጂና የፐልቪክ ፍሎር ሪኮንስትራክሽን ሰርጀሪ የጋይናኮሎጂ ሰብ ስፔሻሊቲ ነው፡፡ ዶ/ር ደብሩ አያይዘውም ከባለቤታቸው ከዶ/ር አና ኪፈር ጋር በመሆን በቀጣዮች ሶስት እና አራት ወራት የ(Feto Maternal Medicine) የስልጠና ፕሮግራም የመክፈት ዕቅድ እንዳላቸውና ይህም ከእናቶች የእርግዝና ወቅት ጤንነት ጋር ተያያዥ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ እነዚህን መሰል ስፔሻሊቲ ፕሮግራሞችን በህክምናው መስክ ማስፋፋት የሀሪቱን የጤና ሁኔታ ማሻሻልና የህብረተሰቡን ጤንነት መጠበቅ የሚያስችል በመሆኑ ተከታታይ ትውልዶችን ሁሉ የሚጠቀም ነው ይላሉ ዶ/ር ደብሩ፡፡
ዶ/ር አና ኪፈር በበኩላቸው ለኢትዮጵያ ባላቸው ፍቅር እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ላይ በቆዩበት ወቅት በተመለከቱት የህክምና መሻሻል በመነቃቃታቸው ይህንን ፕሮግራም ለመጀመር እንደተነሳሱና ይህ ፕሮግራም በሀገሪቱ የእናቶችን ጤና እንክብካቤ ለማሳደግ እጅግ ጠቃሚና መሰረታዊ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ለዶ/ር አና ስለ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውና ስለተመለከቷቸው አጠቃላይ ሁኔታዎች ላቀረብንላቸው ጥያቄ፤ “ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብና አመራሮች ጥልቅ አክብሮት እንዳላቸው፤ ማህበረሰቡ ለስራ ተባባሪ፣ ቅንና እንግዳ አክባሪ መሆናቸውን፣ ቦታውም ለስራ ምቹ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ከባለቤቸው ከዶ/ር ደብሩ ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የአውሮፓ ስታንዳርድ ያለው የህክምና ስርዓተ-ትምህርት ለመቅረፅ (develop) ለማድረግ ዕቅድ እንደላቸውና ይህም ዓለም አቀፍ የትምህርት ጥራትን የጠበቀ እንዲሆን እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡
ከጀርመን ሃገር በተለያዩ ጊዚያት በተለይ በህክምናው ዘርፍ የሚመጡ ዶክተሮች በማስተማርና በህክምና ላይ የሚጉኙ ኢትዮጵያዊ ዶክተሮችን አቅምና ችሎታ እያጎለበቱ እንደሆነ ይህም ዩኒቨርሲቲው ባለው ጠንካራ ዓለም አቀፍ ግንኙነት የተገኘ እንደሆነ የማህፀንና ፅንስ ባለሙያ የሆኑ ዶ/ር ሙላት አደፍርስ ገልፀው ይህንኑ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡
ደምሴ ደስታ
የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

