በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የላፓራስኮፒ(laparascopy) እና ኢንዶስኮፒ(endoscopy) ወርክሾፕ ተካሄደ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የማህፀንና ፅንስ ህክምና ትምህርት ክፍል ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር ከጥቅምት 7/2010 ዓ.ም ጀምሮ ለ5 ተከታታይ ቀናት የቆየ የላፓራስኮፒ (laparascopy)ና ኢንዶስኮፒ(endoscopy) ወርክሾፕ በዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተካሂዷል፡፡
[widgetkit id=7141]
በአሜርካን ሀገር በላፓራስኮፒ(laparascopy)ና ኢንዶስኮፒ(endoscopy) ህክምና የረጅም አመታት ልምድ ባካበቱ ሁለት ባለሙያዎች ዶ/ር ኑሩ አብሴኖ ሮቢ እና ዶ/ር ጆን ጆርጅ ከሀገር ውስጥ ደግሞ በላፓራስኮፒ(laparascopy)ና ኢንዶስኮፒ(endoscopy) ህክምና ስልጠና የወሰዱ ሁለት ባለሙያዎች ዶ/ር እስክንድር ከበደ እና ዶ/ር እያሱ ባጠቃላይ በ4 ባለሙያዎች በተሰጠው ስልጠና ከ8 እህትማማች ዩኒቨርሲቲዎች የመጡትን ባለሙያዎች ጨምሮ ባጠቃላይ 17 የማህፀንና ፅንስ ህክምና ሀኪሞች ተሳትፈዋል፡፡
ኢንዶስኮፒ(endoscopy) ህክምና የማህፀንና ፅንስ ችግር ያለባቸውንና ለረጅም አመታት መውለድ ያልቻሉ እናቶችን ማህፀን በማየት የማህፀን እጢና የዘር ፍሬ ችግር መኖር አለመኖሩን፣ የእንቁላል ማለፊያ ቱቦ ትክክል መሆኑንና አለመሆኑ እንዲሁም ሌሎች ችግሮችን ቁልጭ አድረጎ የሚያሳይ መሳሪያ ሲሆን፣ ላፓራስኮፒ (laparascopy) ደግሞ ሆድ ሳይከፈት የተጎዳውን የሰውነት ክፍል በቀዶ ጥገና ማስተካከል የሚቻልበት የህክምና አይነት ነው፡፡ በዚህም በቪዲዮ ካሜራ በመታገዝ ሆድ ሳይከፈት ምርመራና ቀዶ ህክምና የሚደረግ ሲሆን፡ በቀዶ ህክምናው የሚኖረው ጠባሳ በጣም ትንሽ እንደሚሆንና በሽተኛው ቶሎ በማገገም በሆስፒታል የሚቆይበትን ጊዜ እንደሚያሳጥር በስልጠናው ወቅት ተገልጿል፡፡
የዚህ ዎርክ ሾፕ ዋና አላማ፣ በዚህ ህክምና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች እውቀታቸውን የሚያካፍሉበት(የክህሎት ሽግግር የሚያደርጉበት) እና ጎን ለጎን ለበሽተኖች ህክምናው የሚሰጥበት መሆኑን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህፀንና ፅንስ ህክምና ስፔሻሊስት ሀኪም እና የስልጠናው አስተባባሪ ዶ/ር ሙላት አደፍርስ ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር ሙላት አያይዘውም ይህን መሰል ስልጠና ከዚህ ቀደም በሀገር አቀፍ ደረጃ ተሰጥቶ እንደማያውቅ እና ወደፊት ዩኒቨርሲቲውን በማህፀንና ፅንስ ህክምና የልህቀት ማእከል እንዲሆን ቀጣይነት ያላቸው ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የቀድሞ ተማሪ እና በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካን ሀገር በማህፀንና ፅንስ ህክምና ላይ በመስራት የሚገኙት ዶ/ር ኑሩ አብሴኖ ሮቢ የዚህ ፕሮግራም አሰልጣኝ ናቸው፡፡ ዶ/ር ኑሩ ስለ ስልጠናው ሲናገሩ ”አላማችን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በላፓሮስኮፒ ቀዶ ጥገና የልህቀት ማዕከል እንዲሆን ስለሆነ እዚህ ያሉ ሀኪሞች እራሳቸውን ችለው እስከሚሰሩ ድረስ ሙያዊ ድጋፍ መስጠታችንን እንቀጥላለን” ብለዋል፡፡
በዚህ ስልጠና ባለሙያዎች ህክምናውን በቋሚነት ለመስጠት የሚያስችላቸውን አዳዲስ እውቀት እያገኙና መሳሪያዎችንም እየተዋወቁ ይገኛሉ ያሉት ደግሞ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የማህፀንና ፅንስ ህክምና ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶ/ር የሽዋስ አበበ ናቸው ፡፡ በተጨማሪም ደ/ር የሽዋስ በተግባር የተደገፈና አዳዲስ ቴክኖሎጅዎችን የሚያስተዋውቅ እና መሰል ስልጠና መሰጠቱ በዩኒቨርሲቲው ለሚሰጠው ጥራት ያለው ትምህርት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ካነጋገርናቸው ሰልጣኞች መካከል ዶ/ር አቤል ተሸመ ስልጠናው አስመልክቶ ሲናገሩ “ስልጠናው በጣም ጠቃሚና አዳዲስ እውቀቶችን ያገኘንበት ቢሆንም የስልጠና ጊዜው ትንሽ ረዘም ላለ ጊዜ ቢሰጥና ስልጠናው ቀጣይነት ቢኖረው” ሲሉ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
ዘጋቢ- መሰረት አልምነህ
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

