በጎንደር ዩኒቨርሲቲ 10ኛው የቱሪዝም ሳምንት በዓል በድምቀት ተከበረ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የቱሪዝም ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል የሚዘጋጀው አመታዊ የቱሪዝም ሳምንት በዓል ለ10ኛ ጊዜ በድምቀት ተከበረ፡፡ ከጥር 1 አስከ ጥር 5/2009 ዓ.ም “የቱሪዝም ተደራሽነት ለሁሉም” በሚል መሪ ቃል ለአምስት ተከታታይ ቀናት በተለያዩ አዝናኝና አስተማሪ ዝግጅቶች በጎንደር ዩኒቨርስቲ ግቢ ተከብሯል፡፡ በዓሉ በቱሪዝም ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል፣ በጎንደር ከተማ አስተዳደር እና በሰሜን ጎንደር ዞን ባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች የጋር ትብብር የተዘጋጀ ነበር፡፡

በበዓሉ የመክፈቻ ስነስርዓት ላይ አቶ አሸብር ተክሌ፤ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ተቋም ዋና ዳይሬክተር፣ ዶ/ር ሂሩት ካሰው፤ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቢሮ ኃላፊ፣ ወ/ሮ የትነበርሽ ንጉሴ፤ የብርሀን ለዓለም አለማቀፍ አማካሪ፣ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞችና ተማሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ በመክፈቻ ስነስርዓቱ በአሁኑ ጊዜ አገራዊ ልማትን በመደገፍና በማፋጠን ረገድ ለዓለም ሀገራት ትልቅ የኢኮኖሚ ፋይዳ ያለው የቱሪዝም ኢንዱስትሪን፣ ሀገራችን ተጠቃሚ በምትሆንበት መልኩ ለመስራትና በዘርፉ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የሚረዳ የቱሪዝም አስተዳደር ትምህርት ክፍል በመክፈትና ለዘርፉ እድገት ከፍተኛ ድርሻ ያላቸውን ባለሙያዎች በማፍራት ዩኒቨርሲቲው ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ይህ በዓል በነዚህ አስር ዓመታት ውስጥ በቱሪዝም ባለድርሻ አካላት መካከል ያለውን ግንኙነት በማሳደግና የአጋር አካላትን ተሳትፎ በመጨመር ከከተማችን ጎንደር እሰከ ሀገር አቀፍ ተቋማት የሚሳተፉበት ታለቅ በዓል ለመሆን መብቃቱንና ይህም ለቱሪዝም ዕድገት ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡

በመጨረሻም የዘንድሮው የቱሪዝም ሳምንት በዓል፣ ክብረ በዓሉ 10ኛ ዓመቱን የደፈነበት ልዩ በዓል በመሆኑ ለትምህርት ክፍሉ መምህራን፣ ተማሪዎችና ሰራተኞች እንዲሁም ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የእንኳን አደረሳችሁ መልክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የበዓሉ አንዱ አካል በነበረው ትምህርታዊ ጉባኤ ላይ በርካታ ጥናታዊ ፁሁፎች በዩኒቨርሲቲው መመህራንና በተጋባዥ እንግዶች የቀረቡ ሲሆን በጥናታዊ ፁሁፎች ዙሪያም ውይይት ተካሂደዋል፡፡ ከቀረቡት ጥናታዊ ፁሁፎች መካከልም በአገልግሎት መስጫ ተቋማትና የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች ለአካል ጉዳተኞች፣ በዕድሜ ምክንያት የመንቀሳቀስ ችግር ላለባቸው ተገልጋዮች፣ ለነብሰጡር ሴቶች፣ ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ለሚጓጓዙና በማንኛውም ሁኔታ የመንቀሳቀስ፣ የመስማትና የማየት ችግር ላለባቸው ተገልጋዮች የተመቹ እንዲሆኑ የሚገልፅ የግንዛቤ ማስጨበጫ ጽሁፍ በወ/ሮ የትነበርሽ ንጉሴ ቀርቧል፡፡ ጥናቱም ከመሪ ቃሉ ጋር ተያያዝነት ያለው በመሆኑ መሪ ቃሉ የተመረጠበት ዋነኛ ምክንያት የቱሪዝም መስጫ ተቋማትና የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች፤ ተገልጋዮች በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ በምቾትና በእኩልነት የሚጠቀሙባቸው ቦታዎች መሆን እንደሚገባቸው ለማሳየት መሆኑም በበዓሉ ተገልጿል፡፡

በክብረ በዓሉም በጎንደር ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የቱሪዝምና ሆቴል አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ማለትም ሆቴሎች፣ ካፌዎችና ሬስቶራንቶች የሚያዘጋጇቸውን ባህላዊና ዘመናዊ ምግቦች በኤግዚቪሽኑ በማቅረብና በቅምሻ ውድድር በመሳተፍ አቅማቸውን አሳይተዋል፡፡ በዚህም በዘመናዊ የምግብ ዝግጅት ውድድር ፍሎሪዳ ኢንተርናሽናል ሆቴል አንደኛ ሲሆነ፤ ሩት ሆቴልና ኤጅ ሆቴል በተከታታይ የሁለተኝኘነትንና ሦስተኝነትን ደረጃ አግኝተዋል፡፡

በባህላዊ የምግብ ዝግጅት ደግሞ ቀዳሚውን ደረጃ ቆብ አስጥል ባህላዊ ምግብ ቤት ሲይዝ ጃን ተከል ሆቴልና ዳውን ታውን ኪውንስ ሆቴል በቅደም ተከተል ተከታዮችን ደረጃ ይዘዋል፡፡ በኬክ ውድድር ፍሎሪዳ ኢንተርናሽናል ሆቴል አንደኛ ሲሆን ጃንተከል ሆቴልና ላንድማርክ ሆቴልም የሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ተቀናጅተዋል፡፡ ቸኮሌት ትሪ ካፌና ኮፊ ሀውስ ልዩ ልዩ ጣእም እና መዓዛ ያላቸውን ኬኮች በማቅረብ ዘርፍ አሸናፊ ሆነዋል፡፡ እነዚህ ተቋማትም ለተሳታፊነታቸው ከዩኒቨርሲቲው የምስጋና የምስክር ወረቀት እንዲሁም ለአሸናፊዎች ደግሞ የዋንጫ ሽልማት ተሰጥቷቸዋልዋል፡፡

ተማሪዎችም በፋሽን ዲዛይን ስራ፣ በዳንስ፣ በድምፅ፣ በቁንጅና ውድድርና በሌሎችም ዝግጅቶች በመሳተፍ ከትምህርት ውጭ ያላቸውን አቅምና ተሰጥኦ በማሳየት ተሳትፈዋል፡፡
ይህ የቱሪዝም ሳምንት በዓልም መታሰቢያነቱን፣ በተፈጥሮ ቅርስ በብቸኝነት የተመዘገበውን የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን ለመጠበቅና የተጋረጠበትን ችግር ለማስወገድ የማይተካ ስራ እየሰራ ለሚገኘው፣ ለኦስትሪያ የልማት ትብብር ግብረሰናይ ድርጅት አድርጓል፡፡ ድርጅቱ ለቱሪዝምና ሌሎች ማህበረሰብ አቀፍ ስራዎች ላበረከተው አስተዋፅኦ ዕውቅና ለመስጠት የታሰበ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በአጠቃላይ በዓሉ በታዋቂ ድምፃውያን ጣዕመ ዜማ፣ በዩኒቨርስቲው የትያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ተማሪዎች አዝናኝ ጥበባዊ ድግስ የተለያዩ ይዘት ባላቸው የተማሪዎች ውድድር የደመቀ ነበር፡፡



