በጥናታዊ ፅሁፍ ዙሪያ ሴሚናር ተካሄደ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የድህረ-ምረቃ ፕሮግራሞች ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት ‹‹the post graduate journey decoded: how to produce high quality output by fast tracking the research process value chain›› በሚል ርዕስ ፕሮፌሰር ማሞ ሙጨን በመጋበዝ ጥር 4/2010 ዓ.ም ሴሚናር ተካሄደ፡፡ በሴሚናሩ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻን ጨምሮ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ መምህራንና በትምህርት ላይ የሚገኙ የሁለተኛና የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡
[widgetkit id=8079]
ፕሮፌሰር ማሞ ሙጨ ጥናታዊ ፅሁፎችን ስንፅፍ ልንከተላቸው ስለሚገቡ ሂደቶችና ሊካተቱ ስለሚገባቸው ይዘቶች ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በገለፃቸው ለምንፅፈው ጥናታዊ ፅሁፍ ጥራት እና ቀዳሚነት (originality) ትኩረት ልንሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡ ከገለፃቸው በተጨማሪም የሁሉም ትምህርት ዘርፍ የድህረ-ምረቃ ተማሪዎች ህብረት ፈጥረው በጋራ ቢሰሩ ውጤት ያለው ስራ መስራት እንደሚቻል በሌሎች ሀገሮች ያዩትን ተሞክሮ ተናግረው፣ ለህብረቱ መዋቀርና መጠናከርም የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡
በሴሚናሩ የተገኙት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ፣ ዩኒቨርሲቲዎችና በአጠቃላይ የትምህርት ተቋማት ጥናትና ምርምሮችን ማካሄድ ዋና ተልእኳቸው መሆኑን ጠቅሰው ፕሮፌሰር ማሞ ሙጨ ይህን ሴሚናር በማቅረባቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ አያይዘውም ፕሮፌሰር ማሞ ሙጨ በዩኒቨርሲቲያችን የተለያዩ ኮሌጆች ለሴሚናሩ የመወያያ ሀሳብ በማቅረብ ሴሚናሮችን ከማካሄዳቸው ባሻገርም ዩኒቨርሲቲያችን እንደ ቻይና ካሉ አለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ግንኙነት እንዲፈጥርና ተማሪዎቻችን እና መምህሮቻችን ወደእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ሄደው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የሰሩት ስራ እና የዩኒቨርሲቲያችንን አለምአቀፍ ግንኙነቶች ለማጠናከር እየሰሩ ያሉት ስራ የሚመሰገን ነው ብለዋል፡፡
በሴሚናሩ መጨረሻም ተሳታፊ መምህራንና ተማሪዎች በቀረበው ሀሳብ ላይ ተጨማሪ ሀሳቦችን በመስጠት እንዲሁም ጥያቄዎችን በማቅረብ ውይይት ተካሂዶ ሴሚናሩ ተጠናቋል፡፡
ዘጋቢ፡ መሰረት አለምነህ
ህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

