በፆታዊ ጥቃትና በህግ የበላይነት ላይ ያተኮረ ወርክ ሾፕ ተካሄደ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት አዘጋጅነት በፆታዊ ጥቃትና በህግ የበላይነት ላይ ያተኮረ ወርክ ሾፕ በትምህርት ቤቱ ምስለ ችሎት አዳራሽ ህዳር 22/2010 ዓ.ም ተካሄደ፡፡
በወርክ ሾፑ ከአሜሪካ ሲያትል ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ላይቬሪያዊት ፕሮፌሰር ቬሮኒካ ፈይ ፈሩይ ተጋብዘው ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህግ ትምህርት ቤት መምህራንና ተማሪዎች፣ የተለያዩ የትህርት ክፍል መምህራንና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
[widgetkit id=7824]
አቶ አበበ አሰፋ የህግ ትምህርት ቤት ዲን ወርክሾፑን በንግግር ሲከፍቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመማር ማስተማር፣ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ስኬታማ የሆኑ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ በተከታታይ አመታት የሚያገኛቸው ደረጃዎችና ያስመዘገባቸው ውጤቶች ያመላክታሉ ብለዋል፡፡ በትምህርት ቤቱ በኩልም ከሚደረገው ችግር ፈችና ማህበረሰብ ተኮር የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት በተጨማሪ የከፍተኛ ትምህርት የመውጫ ምዘና (EXIT EXAM) የወሰዱ የትምህርት ቤቱን ተማሪዎች 100% ማሳለፉ ትልቅ ስኬት መሆኑን ተናግረው በዚህ ወርክ ሾፕ ልምዳቸውንና እውቀታቸውን ሊያካፍሉ ለመጡት ለፕሮፌሰር ቬሮኒካ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ፕሮፌሰር ቬሮኒካ የህግ የበላይነትን በማክበር፣ የሴት ልጆችን ጥቃት እንዴት እንከላከል የሚል ይዘት ያለው ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡ በፅሁፋቸውም በላይቬሪያ የሚታዩ ፆታዊ ጥቃቶችንና ህጉ ምን ይህል ተግባራዊ እየሆነ ነው የሚለውን ዳስሰዋል፡፡ በጥናታቸው በርካታ ጥቃቶች የደረሱ መሆኑንና ወደ ህግ መድረስ የቻሉት እና ፍትህ ያገጉት ግን እጅግ ጥቂቶች መሆናቸውን ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህም የሆነው ሴቶች ጥቃት ቢደርስባቸውም በማህበረሰቡ የሚደርስባቸውን ጫና በማሰብ የህግ አገልግሎት ወደ የሚሰጥባቸው ተቋማት ለመሄድ እንደማይደፍሩ ጭምር ተናግረዋል፡፡ ፕሮፌሰሯ ባቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፍ መነሻ በማድረግ በኢትዮጵያ በሚታዩ ተመሳሳይ ችግሮች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህግ ትምህርት ቤት በህግ የበላይነትና በሴቶች ጥቃት ዙሪያ የሚሰጠውን የማህበረሰብ አገልግሎትና የሚያከናውናቸውን ችግር ፈች ምርምሮች አጠናክሮ ለማስቀጠልና ልምዶችን ለመውሰድ መሰል ወርክ ሾፖች መካሄዳቸው ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውም በውይይቱ ተገልፆል፡፡
በመጨረሻም በፕሮፌሰር ቬሮኒካ ተቋቁሞ የአፍሪካን ስደተኞች ሰቆቃ እንዴት ማስቆምይቻላል? በሚል እየሰራ የሚገነው ድርጅት ከዩኒቨርሲቲው በተለይ ደግሞ ከህግ ትህርት ቤት ጋር በጋራ ለመስራት ያለውን ፍላጎት ፕሮፌሰሯ ተናግረዋል፡፡ ይህም በመተማ በኩል ያለውን የስደተኞች ጉዞ፣ የህግ የበላይነትን በማስከበር ለመከላከልና የስደተኞችን መብት ለማስከበር ትምህርት ቤቱ ሊሰራ ላሰበው ተግባርና በቅርቡ መተማ ላይ ሊከፈት በታሰበው ነፃ የህግ ድገፍ አገልገሎት ዙሪያም ደድርጁቱ በጥናት ችግሮችን በመለየት ከመንግስታት ጋር በመነጋገርና በሌሎች ድጋፎችም አስተዋፅኦ በማድረግ ለስራቸው መሳካት አጋዥ እንደሚሆን የትምህርት ቤቱ ዲን አቶ አበበ ገልፀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- መሰረት አለምነህ

