ትኩረት ለአካል ጉዳተኛ ህፃናት
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1959 የመንግስታቱ ድርጅት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ዓለም አቀፍ የህፃናት ቀን በኢትዮጵያ በየአመቱ ህዳር 11 ይከበራል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስነ-ትምህርት ፋካልቲ መምህራንም ቀኑን ምክንያት በማድረግ በአዘዞ ቀበሌ 19 ሙሉ ሳይክል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው በዓሉን ከአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ጋር አክብረዋል፡፡
[widgetkit id=7466]
የስነ-ትምህርት ፋኩልቲውና አዘዞ ቀበሌ 19 ሙሉ ሳይክል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባላቸው የጋራ ስምምነት ትምህርት ቤቱን ሞዴል ትምህርት ቤት ለማድረግ በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለአብነትም የመምህራንን አቅም የማጎልበትና የአጫጭርና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎችን የመስጠት፣ ትምህርት ቤቱን በተለያዩ ግብአቶች የመደገፍ እና ሌሎችም የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ህዳር 11/2010 ዓ.ም በአዘዞ ቀበሌ 19 ሙሉ ሳይክል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተከበረው ዓለም አቀፍ የህፃናት ቀን የስነ- ትምህርት ፋኩልቲ ዲን ወ/ሮ መሰረት ሀሰንን ጨምሮ የፋኩልቲው መምህራን፣ የአዘዞ ቀበሌ 19 ሙሉ ሳይክል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህራን፣ መምህራን፣ አይነስውር ተማሪዎችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶችም ተገኝተዋል፡፡ የአካል ጉዳተኛ ህፃናት እንደማንኛውም ህፃናት የመማር የመጫወትና ሌሎችን ነገሮች የማድረግ መብት እንዳላቸው የገለፁት ወ/ሮ መሰረት፣ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን በመማር ማስተማር ሂደቱ የሚያግዙ ግብአቶችም ሊሟሉላቸው ይገባል ብለዋል በመክፈቻ ንግግራቸው፡፡
በዝግጅቱ አይነ ስውር ተማሪዎች የተለያዩ አዝናኝ እና አስተማሪ ፕሮግራሞችን አቅርበዋል፡፡ ተማሪዎቹ ባቀረቡት መልእክት አዘል ጭውውት ትምህርት ቤቶች ለአካል ጉደተኛ ተማሪዎች ምቹ አለመሆናቸውን፣ ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች አስፈላጊ የሆኑ የትምህርት ግብአቶች አለመሟላታቸውን እንዲሁም በማህበረሰቡ ዘንድ ለአካል ጉዳተኞች ያለውን የተሳሳተ አመለካከት ጠቁመዋል፡፡ ዝግጅቱ አይነስውር ተማሪዎች ባቀረቡት የእንኳን ደህና መጣችሁ መዝሙር፣ ግጥም፣ መጣጥፍ እንዲሁም ዜማና ውዝዋዜ ደምቋል፡፡
በመጨረሻም በትምህርት ቤቱ ለሚማሩ አይነ ስውር ተማሪዎች በባትሪና በቻርጅ የሚሰሩ 16 የድምፅ መቅጃ ቴፖች እና 16 ባለ 8GB ፍላሽ ካርዶች ተበርክቶላቸዋል፡፡ እነዚህ የትምህርት አጋዥ መሳሪያዎች ከእስራኤል የውጭ ጉዳይ(Mashav) በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ መገዛቱን የፕሮጀክቱ ባለቤትና በፋኩልቲው የትምህርትና ስራ አመራር ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ ክንዴ አበጀ ገልፀዋል፡፡ ተማሪዎችም በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡
ዘጋቢ፡ መሰረት አለምነህ
ህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

