ነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ለፍትህ አካላት አጋዥ ናቸው ተባለ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት የነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎት መስጫ ማዕከል፣ የነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎት አሰጣጥ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ከአጋር አካላትጋር ታህሳስ 24/2010 ዓ/ም በምስለ ችሎት አዳራሽ ውይይት አደረገ፡፡ በእለቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ፣ ከኤፍድሪ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አቶ ቢኒያም ግደይ፣ ከባህርዳር ቅርንጫፍ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አቶ አበረ ሙጨ፣ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ፈንታሁን፣ የነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ባሉበት ወረዳዎች የመጡ የፍትህ ጽ/ቤት ኃላፊዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡
[widgetkit id=8064]
ፕሮግራሙን በንግግር የከፈቱት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ፣ ተሳታፊ እነግዶቹን በማመስገን ‘’ይህንን የነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎት በ2002 ዓ/ም ስንጀምር ከኤፍድሪ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በተደረገ ድጋፍ ሲሆን፣ የመጀመሪያውን ማእከል ጎንደር ከተማ ከፍተን ነበር፡፡ በአሁኑ ስዓት ወደ 16 የሚሆኑ ማዕከላትን ከፍተን ተማሪዎች፣ መምህራንና የማዕከሉ ሰራተኞች እንደሚሉት ለማይናገሩት እንናገራለን(we are the voice of voiceless) የሚል መርህ ይዘው እራሳቸውን ችለው ፍርድ ቤ ት መቆምም፣ መከላከልም ለማይችሉ ህጻናት፣ አረ ጋዊያን፣ ሌሎች አቅመ-ደካሞች ድምጽ ሆነው እያገለገሉ ናቸው ብለዋል፡፡’’ አያይዘውም ፕሮግራሙ በማዕከሉ ለሚሳተፉ ተማሪዎች የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ገልጸው፣ ተሳታፊዎችን በራሳቸውና ድጋፍ በሚደረግላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ስም አመስግነዋል፡፡
በመቀጠል የዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ቤት ዲን አቶ አበበ አሰፋ፣ የፍትህ ተደራሽነት ለዘላቂ የልማት ግቦች ያለው ሚና፣ የህግ ትምህርት ቤቶች ያላቸው ሚናና የህግ መሰረት በሚል ጥናታዊ ጽሁፍ ሲያቀርቡ፣ የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ደመወዝ ካሴ ደግሞ የማዕከሉን የአፈጻጸም ሪፖርት አቅርበው በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡ ከኤፍድሪ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የመጡት አቶ ቢኒያምም፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ነፃ የህግ ድጋፍ አገልገሎቱን የስትራክቸሩ አንድ አካል አድርጎ መስራቱ፣ ያለው ቁርጠኝነት፣ በአጠቃላይ ያሉትን ችግሮች ተቋቁሞ ቋሚ የህግ ባለሙያ ቀጥሮ እንዲሰራ ማድረጉ ቀዳሚ አፈጻጸም እንዲኖረው አድረጎታል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ድጋፉን እያገኙ ካሉት የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ከጎንደር ከተማ የመጡት አቶ ዘመነ ካሴና ከምእራብ በለሳ ቄስ አሰፋ ተገኘ በእለቱ ተገኝተው ምስክርነታቸውን ገልጸዋል፡፡
በተያያዘ ፕሮግራም ታህሳስ 25/2010 ዓ/ም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ፈንታው፣ የዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ቤት ዲን አቶ አበበ አሰፋ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካል ጉዳት ጥናትና አገልግሎት መስጫ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ህይወት አበበ፣ ከታች አርማጭሆ ወረዳ ከፍትህ ጽ/ቤት፣ከወረዳው ፍርድ ቤት፣ የማዕከሉ ባለሙያዎች፣ ከሴቶችና ህፃናት እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት በተገኙበት 16ኛውን ማዕከል በታች አርማጭሆ ወረዳ ሳንጃ ከተማ በመክፈት ተመርቋል፡፡ በእለቱም ከወረዳው የፍትህ አካላትና ከፕሮግራሙ ጋር ቀጥተኛ አገልግሎት ካላቸው አካላት ጋር ውይይት ተካሂዶ የትክል ድንጋይን ማዕከል በመጎብኘት ፕሮግራሙ ተጠናቋል ፡፡

