አካል ጉዳተኞች በተለያዩ ሙያዎች ሰልጥነው ተመረቁ(የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሲቢአር ፕሮግራም የ25 ሰልጣኞችን ወጭ ሸፍኗል)
የጎንደር አካል ጉዳተኞች ክህሎት ማሰልጠኛ ማዕከል በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስር ከሚገኘው ሲቢአር ፕሮግራምና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር ከተለያዩ አካባቢዎች የተወጣጡ 95 አካል ጉዳተኞችን ለአምስት ወር በተለያዩ ሙያዎች አሰልጥኖ የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ጥር 29/2010 ዓ.ም በደማቅ ሁኔታ አስመረቀ፡፡
በ1963 ዓ.ም የተመሰረተው የጎንደር አካል ጉዳተኞች ክህሎት ማሰልጠኛ ማዕከል ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር በየአምስት ወሩ እያሰለጠነ የሚያስመርቅ በክልሉ የሚገኝ ብቸኛ የአካል ጉዳተኞች ማሰልጠኛ ማዕከል መሆኑን የአብክመ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ም/ ኃላፊ አቶ ጥላሁን መኳንንት በምረቃ ፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ማዕከሉ በክልሉ መንግስት ድጋፍ በተገኘ የ15 ሚሊየን ብር በጀት አዳራሽ፣ ምግብ ቤትና መኝታ ቤት በአዲስ መልክ እያስገነባ እንደሆነና እስከአሁን በተሰራው ስራም አካል ጉዳተኞች እንደማንኛውም ዜጋ በተለያዩ ሙያዎች ስልጥነው አምራችና ተወዳዳሪ ዜጋ እንዲሆኑ ምቹ አጋጣሚዎች እየተፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለአካል ጉዳተኛ ማእከሉ አስተዋጽኦ እያደረጉ ከሚገኙ የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መካከል በተለይ የአልጋና የፍራሽ አቅርቦት በማድረግ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ በመሆኑ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስር ለሚገኘው ሲቢአር /CBR/ ፕሮግራም አቶ ጥላሁን ትልቅ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
[widgetkit id=8395]
የጎንደር አካል ጉዳተኞች ክህሎት ማሰልጠኛ ማዕከል ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሞ አብሮ እየሰራ ነው ያሉት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አካል ጉዳት ጥናትና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የህግ መምህር ወ/ሮ ህይወት አበበ፣ ዩኒቨርሲቲው ለአካል ጉዳተኞች የሚያገለግሉ የማቴሪያል ጥገና ሲያስፈልገው በዚህ ማዕከል ጥገናውን እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲውም በበኩሉ የማእከሉን ሰራኞች አቅም ለማጎልበት በየአመቱ አንድ የሁለተኛ ዲግሪና ሁለት የመጀመሪያ ዲግሪ ነጻ የትምህርት እድል ይሰጣል፤ ከዚህም በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው ለማዕከሉ 250 የሚሆን የአልጋ፣የፍራሽና የትራስ ድጋፍ አድርጓል፡፡ እንዲሁም አሰልጣኝ መምህራን ከሰልጣኝ አካል ጉዳተኞች ጋር የሚግባቡበትን የብሬልና የጃውስ ሶፍት ዌር መሰረታዊ የመግባቢያ ክህሎት ስልጠና በሁለት ዙር ተሰጥቷል፡፡
ከጎንደር አካል ጉዳተኞች ክህሎት ማሰልጠኛ ማዕከል ጋር ብዙ የስራ ትስስር አለን ያሉት የሲ ቢ አር ሰራተኛ የሆኑት አቶ ዘመነ አሰፋ፣ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በየወረዳው አካል ጉዳተኞችን በማህበር በማደራጅት ለድጋፍ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ፕሮግራሙ በዚህ ዙር 25 የሚሆኑ ሰልጣኞችን በማሰልጠን የህክምና፣የትራንስፖርትና የስልጠና ወጭን መሸፈኑን አቶ ዘመነ ገልጸዋል፡፡ እነዲሁም ለእያንዳንዱ አካል ጉዳተኛ ተመራቂ ከስልጠና በኋላ 3000 ብር ያህል ድጋፍ እደሚያደርግም አያይዘው ተናግረዋል፡፡ አካል ጉዳተኞች ተመርቀው ብዙ እንግልት እየደረሰባቸው ነውና እንደተመረቁ በቀጥታ ወደ ስራ የሚያሰማራቸው አካል ያስፈልጋል፤ተመርቀው ስራ ላይ ያልተሰማሩ አካል ጉዳተኞች መኖራቸው በማእከሉ፣ በማህበረሰቡና በአካል ጉዳተኛች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፤ ስለሆነም አካቶ ትግበራን/main streaming/ ተግባራዊ በማድረግ አካል ጉዳተኞች በሰራ የሚታቀፉበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል ሲሉ አቶ ዘመነ አሳስበዋል፡፡
በሲቢአር ፕግራም ድጋፍ በተለያዩ ሙያዎች ከሰለጠኑ 25 ተመራቂ አካል ጉዳተኞች መካከል ከደንቢያ ወረዳ አቶ ንጉሴ ብዙአየሁና የፍቱስራ አሌ ፣ እንዲሁም ከአዘዞ አቤኔዘር መስፍን ይገኙበታል፡፡እነዚህ ተመራቂዎች እንደሚገልጹትም ሲቢአር ከተለያዩ አካባቢዎች አፈላልጎ የመንቀሳቀሻ መሳሪያዎችና የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጎላቸዋል፡፡ በተጨማሪም ለእያንዳንዳቸው 1200ብር ያህል በመክፈል የስልጠናውን ወጭ ስለሸፈነላቸው ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ስለሆነም ይላሉ ተመራቂዎቹ ፣ሰልጥነን መመረቃችን መልካም ነው፤ ነገር ግን በተለያዩ ሙያ መስኮች ተሰማርተንና ራሳችንን ችለን የበኩላችን ሀገራዊ አስተዋጽኦ እስክንወጣ ድረስ አሁንም እንደ ሲቢአር ያሉ አጋር አካላት ከጎናችን ሊለዩ አይገባም በማለት ያሳስባሉ፡፡
“ከአይነ-ስውርነት የሚከፋው እያዩ ራዕይ አልባ ሆኖ መኖር ነው!” እንዳለችው ሄለን ኬለር ሁኔታዎች ከተመቻቹላቸው አካል ጉዳተኞችም እንደማንኛውም ሰው መሆን የሚፈልጉትን አላማ ማሳካት እንደሚችሉ ዛሬ በተለያዩ ሙያዎች ሰልጥነው ያየናቸው ወገኖቻችን ትልቅ ማረጋገጫ ናቸው፡፡
በደስታው ዋኘው
አርታኢ፡
ደምሴ ዳምጤ
እና
ይዳኙ ማንደፍሮ
የህዝብና አለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

