አዲሱ የጎንደር የመጠጥ ውሀና ሳንቴሽን ፕሮጀክት በደማቅ ሁኔታ ተመረቀ
ከ533 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ ተደርጎበት በቆላ ድባ ከተማ የተገነባው አዲሱ የጎንደር ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሀ ፕሮጀክት የጎንደር ከተማንና እንግዶቿን ለቀጣዮቹ አስር አመታት በበቂ ሁኔታ የንጹህ ውሀ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይታመናል፡፡ ፕሮጀክቱ በቀን በአማካይ 17 ሺ ሜትር ኩብ ውሀ ማምረትና ማሰራጨት በመቻሉ 44 በመቶ ብቻ የነበረውን የከተማውን የንጹህ መጠጥ ውሀ ሽፋን ወደ 100% ማድረስ መቻሉን የጎንደር ከተማ ውሀና ፍሳሽ አገልግሎት ጽ/ቤት ዋና ስራ አስኪያጂ አቶ ይርጋ አለሙ ገልጸዋል፡፡ የህዝቡን መሰረታዊ የመጠጥ ውሀ አቅርቦት ጥያቄ በዘላቂነት እንደሚፈታ የታመነበት ይህ ፕሮጀክት ህዳር 11/2010 ዓ.ም በደማቅ ሁኔታ ተመርቆ በይፋ ስራ ጀምሯል፡፡
[widgetkit id=7488]
በምረቃው ወቅት በቦታው በአካል በመገኘት የፕሮጀክቱን ስራ ያስጀመሩት የኢፌዲሪ የውሀ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ሚኒስትር የተከበሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሽ በቀለ እና የዕለቱ የክብር እንግዳ የአማራ ብሔራዊ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የተከበሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ሲሆኑ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻና ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የፌደራል፣ የክልል፣ የዞን እና የከተማ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች፣ የመንግስትና የግል ተቋማት ኃላፊዎች፣ የጎንደር ከተማና አካባቢ የተለያዩ የህብረተሰብ አካላትና ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ብቁ የሆነ የተማረ የሰው ሀይል በማፍራት ለሀገር ከማበርከቱ በተጨማሪ የጎንደር ከተማና ያካባቢው ማህበረሰብ ኑሮ እንዲሻሻል ቀን ከሌት እየሰራ ያለ ተቋም መሆኑ በተግባር የተመሰከረ ነው፡፡ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው አሁን ለምረቃ ለበቃው ለዚህ የመጠጥ ውሀ ፕሮጀክት የ15 ሚሊየን ብር ድጋፍ በማድረጉ፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ በኢፌዲሪ የውሀ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ሚኒስትር በተከበሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሽ የምስጋና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ለፕሮጀክቱ መሳካት የአለም ባንክን ጨምሮ የተለያዩ ሀገር በቀል ድርጅቶችና ግለሶቦች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ተገልጿል፡፡
ፕሮጀክቱ ለፍጻሜ በመብቃቱና ስራ በመጀመሩ ደስታችን ወደር የለውም!
በአምሳሉ ግዛቸው] የህ/ዓ/አ/ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

