አጋፔ( የፍቅር ማዕድ)
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በጎ አድራጊ ተማሪዎች በ2006 ዓ.ም የተመሰረተው አጋፔ የቤተሰብ በጎ አድራጎት ማህበር ያስገነባቸውን 6 የመኖሪያ ቤቶች እና የተለያዩ አልባሳት መጠለያ ለሌላቸው ወገኖች መጋቢት 16/2010 ዓ.ም አበረከተ፡፡
አጋፔ የቤተሰብ በጎ አድራጎት ማህበር ከዚህ በፊት አሰር የሚሆኑ ቤቶችን፣ የተለያዩ አልባሳትንና የመገልገያ ቁሳቁሶችን ለአቅመ ደካማ አረጋውያን መስጠቱ ይታወቃል፡፡ በያዝነው አመትም ሀዋሪያው ጳውሎስ ት/ቤት አካባቢ ያስገነባቸውን ስድስት የመኖሪያ ቤቶችና የተለያዩ አልባሳትን በማበርከት በጎዳና ላይ የሚንገላቱ ወገኖችን ህይወት እየታደገ ይገኛል፡፡
[widgetkit id=8737]
በአሁኑ ዙር በርካታ አቅመ ደካማ አረጋውያን የቤት ባለቤት ሆነዋል፡፡ መጠለያና አልባሳት ከተሰጣቸው መካከል ከቤተክርስቲያን ተጠግተው የሚኖሩ፣ የእንስሳት ኩበት በመሸጥ የሚተዳደሩ፣ በቤት ሰራተኝነት ተቀጥረው ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ ሰዎች ይገኙበታል፡፡ ስለሆነም ከጸሀይና ከውርጭ የሚታደጋቸው መጠለያና አልባሳት ለአበረከቱላቸው የአጋፔ ማህበር አባላት፣ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲና ሌሎች አጋር አካላት ያላቸውን ክብርና ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ከማህበሩ መስራቾች አንዱና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአዕምሮ ህክምና ክፍል መምህር የሆኑት አቶ አለሙ ለማ ፣ “የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ሊስትሮ ሆነው በመስራትና የተለያዩ የገንዘብ ምንጮችን በማፈላለግ በሚገኘው ገቢ ማህበሩ ከዚህ ደረጃ ላይ ደርሷል፣” በማለት የአባለቱን ጥንካሬ አድንቀዋል፡፡ አያይዘውም የቤት መገልገያ ቁሳቁሶች በሙሉ የተገኙት ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ገልጸው አመስግነዋል፡፡ ስለሆነም ዩኒቨርሲቲው አንድም በተማሪዎቹ አንድም በቁሳቁስ ድጋፍ ለማህበሩ እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን የማህበሩ ሰብሳቢ ገልጸዋል፡፡
የዞብል ክ/ከተማ ተወካይ ማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ፍስሃ ሙሉአለም ክ/ከተማው ለአረጋውያን የቤት ግንባታ የሚሆን 2000 ካሬ ሜትር መሬት በማዘጋጀትና የግንባታ ቁሳቁስ በማቅረብ ለማህበሩ ድጋፍ ማድረጉን በጉባዔው ላይ ገልጸዋል፡፡
የማህበሩ ም/ፕሬዚዳንት ፣ ወጣት አቤል ተሰማ ፣ “እስከዛሬ ጫማ በማጽዳት፣ ፊልም በማሳየትና ስፖንሰር በማፈላለግ ገቢ ስናሰባስብ ነበር ፡፡ አሁን ደግሞ ከገብርኤል ክ/ከተማ መሬት ለመረከብ በሂደት ላይ ነን፡፡ መሬቱን ከተረከብን በኋላ ሻወርና ፑል ቤት በመስራት የተሻለ ገቢ ለማሰባሰብ አቅደናል፣” ሲል የማህበሩን እንቅስቃሴ ገልጧል፡፡
የማህበሩን አመሰራረት አስመልክቶም አስር የሚሆኑ የህክምና ተማሪዎች በ2006 ዓ.ም ጓዳኛቸው ሲታመምባቸው እርሱን ለማሳከም ገንዘብ በማዋጣት የተጀመረው በጎ ስራ አድጎ፣ ዛሬ 300 የሚሆኑ አባላትን ያቀፈ ማህበር መመስረቱን ም/ፕሬዚዳንቱ ተናግሯል፡፡ ስለሆነም “ከተባበርን አቅመ ደካሞችን ለመርዳት እንበቃለን!” በማለት አቤል መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር፣ አቶ ሰለሞን ፈንታው፣ “በምድራችን ከሰው በላይ ለሰው የሚያስፈልግ የለም!” በማለት የአጋፔ ማህበር አባላት ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን ወገኖች በማሰባሰብ ለመጠለያ እንዲበቁ ማድረጋቸውን አመስግነዋል፡፡ አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው ማህበረሰቡን ለመርዳት አላማ እስካለው ድረስ የአጋፔ በጎ አድራጎት ማህበርን ለመርዳት ሁሌም ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነውና ሁላችንም ብንተባበር ደጋፊ የሌላቸውን ወገኖች በተለያዬ መልኩ መርዳት እንደምንችል ከአጋፔዎች ብዙ እንማራለን፡፡
በደስታው ዋኘው
የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

