ከመገጭ እስከ ጣና ብሎም ታላቁ የህዳሴ ግድብ ድረስ ፋይዳ ያለው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ
ከአመታት በፊት በጎንደር ዙሪያ ወረዳ በዳዋ ዳሞት ቀበሌ የተጀመረው የአፈርና የውኃ ጥበቃ ስራ ወደ ሌሎች ቀበሌዎች ተስፋፍቶ በርካታ ተራሮች ከመራቆት እያገገሙ ይገኛሉ፡፡
[widgetkit id=7570]
ይህ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት የተጀመረው በዳዋ ዳሞት የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ሲያስተምር በነበረ አንድ መምሀር አስተባባሪነት ነበር፡፡የዚያን ጊዜው መምህር የአሁኑ ሱፐርቫይዘር አቶ አስናቀው አብተው እና ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚገልፁት ት/ቤቱም ሆነ አካባቢው በጣም የተራቆተ ነበር፡፡ይህንን ጅምር ከፍ እንዲል ለማድረግ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለአካባቢው ህዝብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በመስጠትና ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል፡፡ በትምህርት ቤቱ ብሎም በቀበሌው የመገጭ ወንዝ ተፋሰስን መሰረት አድርጎ እየተሰራ ያለውን የእጽዋትና የአፈር ጥበቃ ለመጎብኘት የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ተመራማሪ መምህራን ህዳር 12/2010 ዓ.ም ወደ ስፍራው አምርተዋል፡፡ የዳዋ ዳሞት ቀበሌ አስተዳዳሪ አቶ ማሩ መሰለ እንዳሉት በመምህር አስናቀውና በዩኒቨርሲቲው ትብብር በት/ቤት ደረጃ የተሰራው ስራ ለተማሪዎች ምቹ የመማሪያ አካባቢ ከመፍጠሩም በላይ ለአካባቢው ጥሩ ምሳሌ በመሆኑ በቀበሌው የሚገኙ ተራራዎች በአንጻሩ በደን ተሸፍነዋል፤ይህም ከፍተኛ የሆነ የውኃ መሸርሸርን እየቀነሰ ይገኛል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ እና የዩኒቨርሲቲው መምህርና የአየር ንብረት ለውጥ ምርምር ማዕከል “የሞዴሊንግና ዳታ ማኔጅመንት” ባለሙያ አቶ ደረጀ አመነ በሰጡት ተመሳሳይ ሳይንሳዊ ማብራሪያ መሰረትም መጋቢ ወንዞቹ ላይ እየተሰራ ያለው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የመገጭ ግድብ ፣የጣና ሀይቅ ብሎም የታላቁ ህዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ ከዚህ ጋር አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው ተጨማሪ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን በመስጠትና ችግኞችን ለአካባቢው በማቅረብ ትብብር እንዲሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
በደስታው ዋኘው
አርታኢ፡ ይዳኙ ማንደፍሮ
የህ/ዓ/ አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

