ከ30 ዓመት በኋላ ወደ እናት ትምህርት ቤታቸው በትዝታ የተመለሱ ሐኪሞች
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የ2ኛው ዙር የህክምና ተማሪዎች ከተመረቁ ከ30 ዓመታት በኋላ ከመላው ዓለም ተሰባስበው ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመምጣት 30ኛ አመታቸውን በድምቀት አከበሩ፡፡
በ1947 ዓ.ም የህዝብ ጤና አጠባበቅ ኮሌጅና የማስልጠኛ ማዕከል በጎንደር ሆስፒታል የጤና ሙያተኞችን በቀዳሚነት ለማፍራት የተቋቋመ ሲሆን በወቅቱ የጤና መኮነን ፤ ነርስና ፤ጤና ተቆጣጣሪዎችን በማስልጠን የተወሰኑ አመታት ካሳለፉ በኋላ በ1971 ዓ.ም የህክምና ትምህርት እንዲሰጥበት ሲደረግ ስያሜው የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሆነ፤ ይህ በሆነ በዓመቱ ማለትም በ1972 ዓ.ም የ2ኛው ዙር የህክምና ተማሪዎች ተቀብሎ ማስተማር ጀመረ እነዚህ ተማሪዎችን በ1985 እ.ኤ.አ (በ1978 ዓ.ም) የተመረቁ ናቸው፡፡ ከተመረቁ በኋላም እንደ ሁኔታው በሀገር ውሰጥና በውጭ ሀገር በተለያዩ እርከኖች በሙያቸው እየሰሩ የሚገኙ ሲሆን፤ በጋራ ተመካክረው 30ኛ ዓመታቸውን በእናት ትምህርት ቤታቸው ለማክበር 30 ያህል የያኔው ምሩቃን መስከረም 29/2008 ዓ.ም በህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቅጥር ግቢ ተገኙ፡፡
በዕለቱ የዛን ወቅት የህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ፕ/ር ማለደ ማሩ በክብር እንግድነት ተጋብዘው የተገኙ ሲሆን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ የህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ደ/ር ሲሳይ ይፍሩ ፤ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራንና ተማሪዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

1985 እ.ኤ.አ ተመራቂዎች የ30ኛ ዓመት በዓላቸውን በኮሌጁ ቅጥር ግቢ ባከበሩበት ወቅት ዶ/ር ፍቅር መለሰ እና ዶ/ር እያሱ ሀብቴ የበዕሉ አስተባባሪ ኮሚቴን በመወከል ንግግር አድረገዋል፡፡ በንግግራቸውም አስተምሮ እዚህ ባደረሰን ት/ቤታችን ግቢ ከ30 ዓመታት በኋላ በመገናኘታችን እጅግ በጣም ደስታ ተሰምቶናል፤ ያሉ ሲሆን ሃሳባቸው እንዲሳካ የዩኒቨርሰቲውና የኮሌጁ አመራሮች ላደረጉላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅረበዋል፡፡ በመቀጠልም በተማሪነት ዘመናቸው የነበራባቸውን የመፅሀፍ እጥረት አስታውሰው ለግዜውም ቢሆን ብር አንድ መቶ ሺህ /1000 ሺህ/ የሚያወጣ አዳዲስና ውድ የህክምና መፅሀፍትን ገዝተው በማምጣት ለኮሌጁ አበርክተዋል፡፡ ዶ/ር እያሱ ሀብቴ በአጠቃላይ የዛን ዘመን ምሩቃንን በመወከል ወደፊት ከዩኒቨርሲቲው ብሎም ከኮሌጁ ጋር በቅርበት በመስራት ትርጉም ያለው መማር ማስተማሩን የሚደገፍ ተግባር ለማከናወን ኮሜቴ መቋቋሙን ገልፀው፤ ሰው እንድንሆን እናት ኮሌጃችን የሰጠችንን መልሰን ዋጋውን ልንከፍል ተዘጋጅተናል ብለዋል፡፡
በበዓሉ ላይ የተገኙት 30ዎቹ የ1985 ምሩቃን ከተመረቁ ዕለት ጀምሮ ለ30 ዓመታት ያለፉባቸውን መንገዶችና አሁን ላሉበት ደረጃ ለመድረስ የነበራቸውን ቁርጠኝነት ለተማሪዎች እና ለበዓሉ ታዳሚዎች ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱና የህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሲሳይ ይፍሩ ለ2ኛው ዙር የህክምና ተማሪዎች እንኳን ወደ እናት ት/ቤታቸሁ በሰላም መጣችሁ ያሏቸው ሲሆን፣በምሩቃኖቻችን የበለጠ በመታገዝ ያለንን አጠቃላይ የዕድገት ጉዞ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የአልሙናይ ዳይሬክቶሬት በማቋቋም በዚህ ረገድ ሰፊ ስራ ለመስራት ጅመር ላይ ባለንበት ወቅት ከመከካከላችን ለተገኛችሁ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል፡፡ ጅምር እንቅስቃሲያችሁ ውጤታማ ስራ መስራት እንደምትችሉ አመልካች በመሆኑ ለሀሳባችሁ ከፍተኛ ክብር አለን ብለዋል፡፡ ፕሬዘዳንቱንና የኮሌጁን ዲን ሲጀምር በ50 ተማሪዎችና በ3 ፕሮግራሞች በአንድ ግቢ የጀመረው ስልጠና በአሁኑ ስዓት ከ30ሺህ በላይ ተማሪዎችንና ከ65 በላይ ቅድመ ምሩቃን ከ78 በላይ ድህረ ምረቃ ፕሮግራም መድረሱን ከኬጅ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርት የሚሰጥበት የኮሚኒቲ ት/ቤትና ከ620 በላይ የመምህራን መኖሪያ አፓርተማ ጨምሮ 7 ግቢዎች ዩኒቨርሲቲው ያለው መሆኑን፣ በአጠቃላይ መንግስት ለከፍተኛ ትምህርት በሰጠው ትኩረት ዩኒቨርሲቲው በከፍተኛ የዕድገት እና የለውጥ ሂደት ላይ መገኘቱን በስላይድ በመደገፍ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ምሩቃኑ የ1985 ምሩቃን ፎቶ በትልቁ አሰርተው በፍሬም በማድረግ ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት እና ለኮሌጁ ዲን በዕለቱ በክብር እንግድነት በተገኙት ፕሮፌሰር ማለደ ማሩ አማካኝነት በስጦታ አቅረበዋል፡፡

በመጨረሻም በ1972 ዓ.ም የ2ኛው ዙር ተማሪዎች ወደ ኮሌጅ ሲመጡ ዲን የነበሩትና በክብር ተጋብዘው የተገኙት ፕሮፌሰር ማለደ ማሩ፤ ያን ጊዜ ተመራቂዎች ከ30 ዓመታት በኋላ ከመላው አለም ተሰባስበው ወደ ኮሌጅ መመለሳቸውን በማየታቸውና በበዓሉ ላይ በክብር በመጋበዛቸው ምሩቃንን አመስግነዋል፡፡ ያን ዘመን ኮሌጁ የህክምና ትምህርት ሲጀምር የነበረውን ፈተናና ፈተናውን ለማለፍ እሳቸው እንደ አመራር፤ መምህራንና ተማሪዎች ጭምር የከፈሉትን እልህ አስጨራሽ ዋጋ በትዝታ የኋልዮሽ ተጉዘው አንስተው፣ ያሁሉ አልፎ ተማሪዎቻቸው በዓለም ዙሪያ የሙያ ቁንጮ ላይ ደርሰው መመልከት በመቻላቸው ታላቅ ኩራት እንደሚሰማቸው ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም ዛሬ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የደረሰበትን ደረጃ ሲመለከቱ ተቋሙ ብቻ ሳይሆን አገራችን በከፍተኛ ዕድገት ላይ ለመገኘቷ ሁነኛ ማመለካቻ መሆኑን፤ ያአሁኑ ትውልዶች ይህንን የተሟላ ሊባል የሚችል አጋጣሚ ተጠቅመውና እንዲህ ፈተናውን በፅናት አልፈዉ ውጤታማ ከሆኑ ቀደምት ምሩቃን ልምድ ቀስመው የበለጠ ለውጤታማነት እንዲተጉ አሳስበዋል፡፡

የጎንደር ዩኒ
ቨርሲቲ
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶት

