ዓለም አቀፍ የእብድ ውሻ በሽታ ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች ተከበረ፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ዓለም አቀፍ የእብድ ውሻ በሽታ ቀንን ለ3ኛ ጊዜ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት በማድረግ እና ቤት ለቤት በመዘዋወር ውሾችን በመከተብ ጥቅምት 26/2010 ዓ.ም አክብሮ ውሏል፡፡
[widgetkit id=7227]
የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቱ ከኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ኢንስቲትዩት ከመጡ ሙያተኞች፣ በጎንደር ከተማ አስተዳደር ከሚገኙ የህክምና ባለሞያዎች እና ከሚመለከታቸው ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተደርጓል፡፡ ውይይቱ የተካሄደው በጎንደር ከተማ ሲኒማ አዳራሽ ሲሆን፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንትን በመወከል የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ህትመት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ዘውዱ ተሾመ በቦታው ተገኝተዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የእንስሳት ህክምና ዲን ዶ/ር ጸጋው ፈንቴ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው እንደገለጹት፣ ዓለም አቀፍ የእብድ ውሻ ቀን የሚከበረው በየአመቱ መስከረም 18 ቀን ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ዘግይተን ጥቅምት 26 ልናከብር ችለናል ብለዋል፡፡ ዶ/ር ጸጋው የእብድ ውሻ በሽታ እጅግ አስከፊ ከሚባሉ በሽታዎች አንዱ መሆኑን አውስተው የውይይቱ ዋና አላማ ማህበረሰቡ በሽታውን እንዴት መከላከል እንደሚቻል ለማስተማር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ተወካይ እና የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ህትመት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ዘውዱ ተሾመ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት፣ የእብድ ውሻ በሽታ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ አሳሳቢ በሽታ መሆኑን ተረድቶ የዩኒቨርሲቲው የእንስሳት ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ከባለድርሻ አካላት ጋር በተግባር የተደገፈ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት በማዘጋጀቱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ እንዲሁም ከዚህ ጋር በተያያዘና መሰል ውይይት ከጎንደር ከተማ አስተዳደር ጋር እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
በውይይቱ ከኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ በሆኑት በዶ/ር ባየ አሸናፊ እና በእንሳት ህክምና ኮሌጅ ም/ዲን በዶ/ር አርዓያ መንግስቱ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በመቀጠል ተሳታፊዎችን አሳታፊ ያደረገ እና ስለ እብድ ውሻ በሽታ መረጃ የሚሰጥ የጥያቄና መልስ ውድድር በዶ/ር አሸናፊ አሰፋ ቀርቧል፡፡
በመጨረሻም በጎንደር ከተማ አስተዳደር በአርበኞች ክፍለ ከተማ የሚገኙ ውሾችን በመከተብ ዓለም አቀፍ የእብድ ውሻ በሽታ ቀን በዓሉ ተጠናቋል፡፡
በግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ሙያተኞች በውይይቱ ላይ ሰፊ ትምህርት እና ቁም ነገሮችን እንዳገኙ ገልጸዋል፡፡ ውሾቻቸውን ያስከተቡ የአርበኞች ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቤታቸው ድረስ በመሄድ ላደረገላቸው ድጋፍ ከፍ ያለ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ድርጊቱ ዩኒቨርሲቲው ሁልግዜም ከማህበረሰቡ ጎን መቆሙን የሚያረጋግጥ ነውም ብለዋል፡፡
በአማሳሉ ግዛቸው
የህ/ዓ/ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

