ዓለም አቀፍ የጸረ – ሙስና ቀን በድምቀት ተከበረ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስነ-ምግባርና ጸረ ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ከፌደራል ስነ ምግባርና ጸረ- ሙስና ኮሚሽን ጋር በመተባበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ14ኛ ጊዜ፣ በሀገር ደረጃ ለ10ኛ ጊዜ፣ በዩኒቨርሲቲው ደግሞ ለ9ኛ ጊዜ “ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመዋጋትም ሆነ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ሁሉም ዜጋ ዘብ ይቁም” በሚል መሪ ቃል መጋቢት 20/2010 ዓ.ም በዩንቨርሲቲው ሳይንስ አምባ አዳራሽ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ም/ፕሬዝዳንትና የፕሬዚዳንቱ ተወካይ ዶ/ር አስራት ዓጸደወይን፣ የፌደራል የስነ-ምግባርና የጸረ- ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አየልኝ ሙሉአለም፣ የአማራ ክልል የስነ-ምግባርና ፀረ- ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ እውነቱ አለነ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስነ- ምግባርና ፀረ- ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ካሳ ተሾመ፣ በሀገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የስነ- ምግባርና ፀረ- ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬቶች ዳይሬክተሮች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ሌሎች የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራንና ተማሪዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና አረጋውያን እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በዝግጅቱ ታድመዋል፡፡
[widgetkit id=8809]
መረሀ ግብሩ የጀመረው የዩኒቨርሲቲውን ግቢ በማጽዳትና ቆሻሻ በማቃጠል ሲሆን የጽዳትና ቆሻሻ ማቃጠል ዘመቻው ተምሳሌትነቱ አዕምሮን ከሙስናና ከብልሹ አሰራር ማጽዳትን ለማሳየት መሆኑን የዩንቨርሲቲው የስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ካሳ ተሸመ ተናግረዋል፡፡ ከሰዓት በኋላ የፓናል ውይይቱ የተካሔደ ሲሆን አቶ ካሳ ለእንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሚያከናውናቸውን ዘርፈ ብዙ ደረጃቸውን የጠበቁ ተግባራት ከጊዜ ወደ ጊዜ በአይነትም ሆነ በመጠን እያሳደገ በመምጣት የተጣለበትን ማህበራዊና ተቋማዊ ሀላፊነቱን በዳይሬክቶሬቱ በኩል እየተወጣ እንደሚገኝ በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸው የጠቆሙት የዩኒቨርሲቲው የስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ካሳ ተሾመ ናቸው፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለውን የሙስና ሰንሰለት ለማዳከምና ለመበጠስ ዳይሬክቶሬቱ በፌደራል መንግስት የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ በሙስናና ስነምግባር ፅንሰ ሀሳብ ዙሪያ የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ በተለያየ መልኩ በማስተማር ስለ ሙስና አጸያፊነት ማስገንዘብ ተችሏል ያሉት አቶ ካሳ በዩኒቨርሲቲው የአሰራር ክፍተት አለባቸው የሚባሉ የተለያዩ ግለሰቦችንና የስራ ክፍሎችን ከማስተካከልና እርምጃ ከመውሰድ በተጨማሪ በፀረ-ሙስና ትግሉ ከፍተኛ ተሳትፎ ለሚያሳዩ የተቋሙ አባላት በየጊዜው እውቅና በመስጠትና በመሸለም እንደሚያበረታቱም ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም የድህነት ምንጭ የሆነውን ሙስናን ለመዋጋት ማንኛውም የህብረተሰብ አካል ርብርብ እንዲያደርግ አቶ ካሳ አሳስበዋል፡፡
“ዩኒቨርሲቲው በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው የፀረ-ሙስና ትግል የሚያደርገውን ተሳትፎ ለማጠናከር፣ ብሎም ተቋሙን ከሙስና የጸዳ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት ከሚያሳይባቸው በርከታ ተግባራት መካከል በየአመቱ የሚከበረው ዓለምአቀፍ የፀረ- ሙስና ቀን አንዱ ነው፡፡ ሙስና የሀገር ኢኮኖሚ እድገት እንዲገታ፣ ኪሳራና ውድቀት እንዲፋጠን በማድረግ፣ ድህነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል፤ የመንግስት ስራዎች ከተገቢው አሰራርና ከህግ ውጪ እንዲከናወኑ ማድረግ ሌላው የሙስና መገለጫ ነው፡፡” ያሉት ደግሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንትና የፕሬዚዳንቱ ተወካይ ዶ/ር አስራት አጸደወይን ናቸው፡፡ ዶ/ር አስራት በመክፈቻ ንግግራቸው አያይዘውም ሙስና እድገትን የሚያቀጭጭና አገራችን የጀመረቻቸውን ዘርፈ ብዙ የእድገት ግቦች ለማሳካት እንቅፋት የሚሆን የህዝብና የሀገር ጠንቀኛ ጠላት በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በጽኑ ሊዋጋው ይገባል ብለዋል፡፡
በስነ ምግባር ጽንሰ ሀሳቦች፣ በአስተዳደራዊ ጉዳዮች፣ በአገር ደረጃ በፀረ- ሙስና ዙሪያ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችና ሙስናን ከመዋጋት አንጻር የሚያጋጥሙ ፈተናዎችና መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች ሶስት ጥናታዊ ጹሁፎች ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጓል፡፡ ሙስናና ብልሹ አሰራርን ከመከላከል አንጻር ንቁ ተሳትፎ ላደረጉ የዩኒቨርሲቲው አባላት የማበረታቻ ሽልማት ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ተወካይ ከዶ/ር አስራት አፀደወይንና ከእለቱ የክብር እንግዳ ከፌደራል ስነምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ከአቶ አየልኝ ሙሉአለም ተበርክቶላቸዋል፡፡
ካነጋገርናቸው የበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የስነ ምግባርና ፀረ- ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዋለ ስጦታው እና የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የስነ ምግባርና ፀረ- ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ላይኩን ብርሀኑ ይገኙበታል፤ እነሱም የቀረቡ ጥናቶችን መሰረት ተደርጎ በተካሄደው ውይይት ጠቃሚ ትምህርቶችን፣ ልምዶችንና ተሞክሮዎችን ማግኘታውን ገልጸዋል፡፡
ዘገባ፡ አምሳሉ ግዛቸው
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

