የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የህክምና ተማሪዎች መስከረም 13/2010 ዓ.ም ተመረቁ
የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ 207 የህክምና ተማሪዎችን ባለፈው መስከረም 13/2010 ዓ.ም በደማቅ ሁኔታ አስመርቋል፡፡
በምረቃ ስነስርዓቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ዶ/ር ከበደ ወርቁ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ፕ/ር አፈወርቅ ካሱ፣ የዩኒቨርሲቲው እና የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሉ የስራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳ እና የጎንደር ከተማ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የተመረቂ ተማሪዎች ወላጆች ተገኝተዋል፡፡
[widgetkit id=6951]
ደ/ር ደሳለኝ መንገሻ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በምረቃ በዓሉ ባደረጉት ንግግር የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከጅምሩ በሀገራችን በቀዳሚነት የጤና ባለሙያዎችን ለማፍራት የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ኮሌጅና ማሰልጠኛ ማዕከል በሚል ስያሜ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1947 ዓ.ም ነበር መሰረቱ የተጣለው፡፡ ይህ ከሆነ ከ63 ዓመታት በላይ እየሆነ ነው፡፡
ዩኒቨርሲቲው በእነዚህ ዓመታት እስከ ማዕከላዊ ዕድሜው የሕዝቡን የጤና ችግር የሚቀርፉ መካከለኛ እና ከፍተኛ የጤና ባለሙያዎችን በማፍራት፤ ወደ ሙሉ ዩኒቨርሲቲነት ከተሸጋገረ ወዲህ ደግሞ ከጤና ሙያተኞች በተጨማሪ በሌሎች ዘርፈ ብዙ ሙያዎች ምሁራንን በማፍራት፣ የሀገራችንን የተማረ የሰዉ ኃይል ፍላጎት በማሟላት ረገድ የበኩሉን ድርሻ በብቃት እየተወጣ ያለ የትምህርት ተቋም ነዉ፡፡ ብለዋል፡፡
የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅን በተመለከተ ዶ/ር ደሳለኝ ሲገልፁ ‹‹ በመማር ማስተማር ረገድ ኮሌጁ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በቅርበት በመነጋገር አገራዊ ፋይዳ ያላቸው 20 የቅድመ ምረቃና 52 የድህረ ምረቃ እና ስፔሻሊቲ ፕሮግራሞችን በመክፈት ለጤናው ዘርፍ የተለያዩ ባለሙያዎችን በማሰልጠን ከፍተኛውን አተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ፤በሀገራችን ከሚገኙ የህክምና ትምህርት ከሚሰጥባቸው ከአንጋፋዎቹ አንዱ የሆነው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለሀገራችን የጤና የዕድገት ጉዞ ለዓመታት ያበረከተዉ አስተዋፅኦ እንዳለ ሆኖ፤ ወደፊትም ከዚህ የተሸለ ውጤት ለማስመዝገብ ጠንከሮ እንደሚሰራ እምነቴ ፅኑ ነው፡፡›› ካሉ በኋላ ኮሌጁ በ2009 ዓ.ም የዓመቱ ምርጥ ኮሌጅ ተብሎ እንዲመረጥ ሁሉም የኮሌጁ ማህበረሰብ ያደረገውን ጥረት አድንቀው፤ ለዚህ መልካም ዉጤታማ ተግባር በርትታችሁ ለሰሩ የኮሌጁ መምህራን፣ በተለያዩ ደረጃ ለሚገኙ አመራሮች፣ ተማሪዎች፣ የጤና ባለሙያዎች እና የአስተዳደር ሰራተኞች በአጠቃላይ ለኮሌጁ እና ለሆስፒታሉ ማህበረሰብ አባላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የእለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ከበደ ወርቁ በንግግቸው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በ1947 ዓ.ም ተነስቶ የነበረውን ወባ በሽታ ወረርሽኝ ለመቆጣጠርና ለማከም የመጀመሪያውን የጤና ጣቢያ በቆላድባ በማቋቋምና የመጀመሪያው የአገራችን የጤና ሙያተኞች ማሰልጠኛ ተቋም በመሆን አገልግሎቱን እንደጀመረ፤ ዩኒቨርሲቲው በየጊዜው እራሱን እያሳደገ ላለፉት 63 ዓመታት በህክምና አገልግሎት፣ የጤና ሳይንስና ሌሎች ተማሪዎችን በማስተማርና በማሰልጠን እንደዚሁም የጤናና ማህበራዊ አገልግሎት ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ በአገራችን ፋና ወጊና ግንባር ቀደም የሆነ ተቋም እንደሆነ እና ከዚህ ተቋም የወጡ ባለሙያዎችም በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች በጤና ተቋማትና በጽ/ቤቶች ውስጥ በመስራት ተፅዕኖ ፈጣሪ በመሆን አገራቸውን እያገለገሉ እንደሚገኙ አውስተዋል፡፡
ዶ/ር ከበደ አያይዘውም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የአምስት ዓመቱ የጤናው ሴክተር የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አካል የሆነውን ወባን በተመረጡ 239 ወረዳዎች ላይ የማጥፋት ዕቅድ (Sub National Malaria Eliminations Plan) በማውጣት ወደ ተግባር መግባቱ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ይህ ተቋም ጎንደር ዩኒቨርሲቲን ማለታቸው ነው ካለው ወባን የመከላከል፣ የማከምና በጥናትና ምርምር ልምድ አንፃር ይህን ትልቅ አገራዊ ዕቅድ ለማሳካት የበኩሉን አስተዋፆ ማድረግ ይጠበቅበታል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ዶ/ር ከበደ በመቀጠልም ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በተጨማሪ ትኩረት የሚሹ የሀሩራማና የቆላ በሽታዎችን በተለይም የካላዛር በሽታን ለመቆጣጠርና ለማከም የሚያገለግሉ የተለያዩ ጥናት እና ምርምሮችን በመስራት አዳዲስ የህክምና ዘይቤዎችንና ዝክረ ሃሳቦችን በመስጠት እያበረከተ ያለው ድርሻ እጅግ የሚደነቅ ለሌሎችም ተቋም አርአያ ሊሆን የሚችል ተግባር ነው ብለዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ረጅም ጊዜ ክትትል የሚፈልጉ chronic illness ችግሮች እንደ ደምግፊትና ስኳር በሽታዎችን የመሳሰሉትን ለማከም የ chronic care model በመፍጠር ህሙማን በአካባቢያቸው በሚገኙ ጤና ተቋማት አገልግሎት እንዲያገኙ ጤና ባለሙያዎችን በመመደብ ከሌሎች የሆስፒታልና የጤና ጣቢያዎች ትስስርና ድጋፍ ጋር በማቀናጀት የሚሰሩ ስራዎች እጅግ አበረታች በመሆናቸው በዚሁ ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ፤በአገራችን በየጊዜው እየጨመረ ያለውን የካንሰር ህሙማንን ቁጥር ታሳቢ በማድረግና የህክምና አገልግሎቱን ተደራሽነት ፍትሃዊ ለማድረግ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የትምህርት ሚኒስቴር በጋራ በመሆን በስድስት በተመረጡ የአገራችን ክፍሎች ላይ የካንሰር ህክምና ማዕከላት በመገንባት አገልግሎቱን ለማስጀመር ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም ማዕከላት ውስጥ አንዱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመሆኑ የዚህን ማዕከል ግንባታ ዩኒቨርሲቲው እያካሄደ የሚገኝ ሲሆን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ግንባታው እንደተጠናቀቀ የዘመናዊ የጨረር ህክምና መሳሪያ (LINAC Radiotherapy) ገዝቶ የሚያቀርብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ የካንሰር ህክምና ተቋም አገልግሎት መስጠት በሚጀምርበት ጊዜ በሰሜን ምዕራብና ምዕራብ አገራችን ለሚኖሩ ዜጎቻችን ተደራሽና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስለሆነ ዩኒቨርሲቲው ለዚህ ማዕከል ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አሳስባለሁ” ብለው ለተመራቂዎች ቀጣዩን የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
” የህክምና ሙያ ከፍተኛ ጥንቃቄና ትዕግስት የሚፈልግ ስራ በመሆኑ ለወደፊቱ በስራ ላይ በምትሰማሩበት ጊዜ ሳይማር ያስተማራችሁን ወገናችሁን በፍፁም የሙያ ስነ-ምግባርና ዲሲፒሊን በቅንነት፤ በርህራሄና በአክብሮት እንድታገለግሉ እየጠየኩ በዚህም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሙሉ ድጋፍ እንደማይለያችሁ ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡ በተጨማሪም ተመርቃችሁ በምትሄዱባቸው የጤና ተቋማት ውስጥ የጤና አገልግሎትና ጥራት ለማስጠበቅ የሚወጡ አገራዊ አሰራርና መመሪያዎችን የሪፎርም ተግባራትና ሌሎች ለአገልግሎቱ አጋዥ ሊሆኑ የሚችሉ መመሪያዎችን ለማስፈፀምና ለመተግበር ግንባር ቀደም መሆን ይገባችኋል፡፡
በዚሁ አጋጣሚ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና የተመራቂ ቤተሰቦች ያደረጋችሁት የብዙ ዓመት ልፋት ውጤት ስላፈራ እንኳን ደስ አላችሁ ፤ለተመራቂ ሀኪሞችም እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሁሉም ኮሌጆች፣ ኢንሰስቲቲዩት፣ ፋካልቲዎችና ትምህርት ቤቶች፣ በመደበኛ፣ በተከታታይና በክረምት መርሃ ግብሮች፣ባጠቃላይ ከ6500 በላይ ተማሪዎችን ከዚህ በፊትማስመረቁ ይታወሳል፡፡

