የምስራቅ በለሳ ጓህላ ሆስፒታል በደማቅ ሁኔታ ተመረቀ
በአማራ ክልል በተለያዩ ወረዳዎች ከተሰሩት የጤና ተቋማት አንዱ የሆነው የምስራቅ በለሳ ጓህላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻን ጨምሮ የተለያዩ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ በተገኙበት ጥር 27/2010 ዓ.ም በደማቅ ሁኔታ ተመርቋል፡፡
የምስራቅ በለሳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጀምበር አያልነህ ሆስፒታሉ ተመርቆ በይፋ ስራ በመጀመሩ የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም በ2008 ዓ.ም በምስ/በለሳ ወረዳ በተከሰተው የዝናብ እጥረት ምክንያት ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለዚህ ወረዳ ብቻ 320 ሺ ብር ያህል ድጋፍ እንዳደረገና ይህም የውሀ አቅርቦት ለማመቻቸት እንደዋለ አብራርተው፣ ከዚህም በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው አዲስ ለተሰራው ሆስፒታል ከጤና ቢሮ ቀጥሎ ከፍተኛውን የሙያና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ያደረገ ተቋም መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ገልፀዋል፡፡
[widgetkit id=8238]
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻም በበኩላቸው በክልሉ መንግስት እየተገነቡ ለሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ዩኒቨርሲቲው በተለያየ መልኩ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝና የጎሀላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን የቁሳቁስ ችግር በተወሰነ ደረጃ ለመፍታትም ከዚህ በፊት ዩኒቨርሲቲው የ1.5 ሚሊየን ብር ማቴሪያል ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡ድጋፍ የሚደረግበት ዋነኛ ምክንያትም ለአዳዲስ ሆስፒታሎች የቁሳቁስ፣የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና በመስጠትና ባለሙያ በመላክ ማህበረሰቡ ለብዙ ስቃይና እንግልት ሳይዳረግ በየአካባቢው የህክምና አገልግሎት እንዲያገኝና በዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሉ የሚስተዋለውን የታካሚዎች ብዛት ለመቀነስ ነው፡፡ ይህም ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሉ ከመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች አቅም በላይ በሆኑ ከባድ በሽታዎች ላይ አትኩሮ እንዲሰራ እንደሚያስችለው ፕሬዚዳንቱ አክለው ገልፀዋል፡፡
በስታንዳርዱ መሰረት ሆስፒታሉ 78 በመቶ ያህሉን የሰው ሀይል ማሟላቱንና ከግብአት አንጻርም ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ከደብረታቦር ሆስፒታልና ከክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ በተገኘ ድጋፍ በመጠኑም ቢሆን ማሟላቱን፣ አቶ ዘመነ ሀብቱ ፣የጎሀላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ስራ አስኪሂያጅ ገልፀዋል፡፡ ሆኖም ተጨማሪ የላቦራቶሪ ቁሳቁሶች ባለመሟላታቸው የህክምና አሰጣጡ ላይ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን አሳስበው፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለሆስፒታሉ የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ስራ አስኪሂያጁ ያላቸውን እምነት ገልፃዋል፡፡
ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አቶ አስፋው ከፍያለው እንደሚሉትም ከዚህ ቀደም በአካባው ጠንካራ የሚባል ጤና ጣቢያ ባለመኖሩ የአካባቢው ነዋሪዎች በተለይ ደግሞ እናቶችና ህጻናት ለህክምና በጎዞ ላይ እያሉ ህይወታቸው ሲያልፍ የነበረበት ሁኔታ ነበር፡፡ ዛሬ የሆስፒታሉ መገንባትና ስራ መጀመር የአካባቢው ነዋሪዎች በቀላሉና በቅርበት ህክምና በማግኘታቸው ከፍተኛ የሆነ እንግልትንና ህይወት ማጣትን እንዳስቀረ ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡ አቶ አስፋው አያይዘውም በሆስፒታሉ የውኃ አቅርቦትና አንዳንድ የላቦራቶሪ ዕቃዎች ሊሟሉ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ሌላው ያነጋርናቸው የምስ/ በላሳ ወረዳ ጤና ጣቢያ ሹፌር ፣አምሳ አለቃ ይታገስ አምባቸው፣ በአካባቢው የጤና ተቋማት እጥረት በመኖሩ ማህበረሰቡ ለዘመናት በበሽታ ሲሰቃይና ለህልፈተ ህይወት ሲዳረግ መኖሩን አስታውሰው አሁን ይህን የመሰለ ሆስፒታል በመገንባቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፡፡ አምሳ አለቃ ይታገስ ከዚህ ጋር አያይዘው ባለፈው አመት በአካባቢው ድርቅ ሲከሰት ለህብረተሰቡ ውኃ በማቅረብ ፈጥኖ የደረሰው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አሁንም የሆስፒታሉን ግብአቶች በማሟላት ጉልህ ድርሻ እንደነበረው ገልጸዋል፡፡ ለወደፊትም በተለይ ሩቅ ቦታ ሄደው መታከም ለማይችሉ ነገር ግን በዚህ ሆስፒታል ታክመው መዳን ለሚችሉ ታካሚዎች ዩኒቨርሲቲው የህክምና ባለሙያዎችን በመላክ እንዲታከሙ ትብብር ቢያደርግ መልካም መሆኑን አምሳ አለቃ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም ለሆስፒታሉ ከዚህ ደረጃ መድረስ ከፍተኛ ሚና ለነበራቸው ለጎንደር ዩኒቨርሲቲና ሌሎች ተቋማትና ግለሰቦች የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
በደስታው ዋኘው
የህ/ዓ/አ/ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

