የሰላምና ልማት ማዕከል/PDC/ ከሌሎች አጋር አካለት ጋር በመተባበር በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዲስ ፕሮግራም ጀመረ
የሰላምና ልማት ማዕከል/PDC/ ከህይወትና ሰላም ኢንስቲትዩት/LPI/፣ከዩ ኤስ ኤይዲ/USAID/ና ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በዩኒቨርሲቲዎች የሰላም እሴቶች ግንባታ ላይ የሚያተኩር የፕሮግራም ማስጀመሪያ ወርክሾፕ ከህዳር 8-10/2010 ዓ.ም አካሄደ፡፡
[widgetkit id=7480]
በወርክ ሾፑ የሰላምና ልማት ማዕከል/PDC/ እና የህይወትና ሰላም ኢንስቲትዩት/LPI/ አስተባባሪዎች፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አመራሮችና በተለያዩ አደረጃጀቶች የሚሰሩ 300 የሚደርሱ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡ “ስለሰላም ማውራት የሚቻለው ሰላም ባለ ጊዜ ነው፤…ማናችንም ብንሆን ማንነታችንን እጅ አውጥተን አንመርጥም፤ የሰላምን ዋጋ ለማወቅ መሞት አይጠበቅብንም ፤በሰላም ማጣት ከተጎዱት ወገኖቻችንና ሀገራት መማር እንጅ…!”በማለት የሰላምን አስፈላጊነት በማብራራት ወርክሾፑን በንግግር የከፈቱት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት፣ ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ፣የፕሮግራሙ በዚህ ዩኒቨርሲቲ መጀመር ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው በአፅንኦት ገልፀዋል፡፡
በተለይ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሰላም እሴቶች ግንባታ ላይ የሚያተኩር ‘‘A Scoping Study Validation for Sustained Dialogue on Ethiopian Campuses’’ በሚል ዳሰሳዊ ጥናት ያቀረቡት የሰላምና ልማት ማዕከል የቁጥጥር፣ግምገማና ምርምር ኤክስፐርት አቶ ንጉሴ አንጌሳ እንደገለፁት የፕሮጀክቱ ዋነኛ አላማ ተማሪዎች በተከታታይ ውይይት/Sustained Dialogue/ በመግባባት ልዩነቶችን እንደ መልካም አጋጣሚዎች በመውሰድ አወንታዊ የተማሪዎች ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ ፕሮግራሙ የሚከተላቸው አምስት ደረጃዎች ማለትም ተማሪዎችን ማደራጀትና አስተባባሪ መምረጥ፣ በየቡድኑ ያሉ ተማሪዎች ማንነታቸውን በነፃነት መግለፅ፣ማንነታቸው ለምን እንደ ችግር ሊሆን ይችላል የሚለውን መለየት፣መፍትሄ መፈለግ፣በልዩነቶች ውስጥ አንድነት መኖሩን ለመግለጽ የጋራ ተግባር ማከናወን መሆናቸውን አስተባባሪዎቹ ያብራራሉ፡፡
ይህ ፕሮግራም በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም መሰል ተግባራትን አከናውኗል፡፡ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለሶስት ቀናት በተከናወነው የፕግራም ማስጀመሪያ/kick off / ተግባር የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው መስቀለቃል ከሌሎች አስተባባሪዎች ጋር በተማሪዎች የጉዞ ፕሮግራም ተገኝተዋል፡፡ የፕሮግራሙ ተሳታፊ ተማሪዎችም ከዩኒቨርሲቲው ግቢዎች እስከ ጎርጎራ ድረስ አብሮ በመጓዝና የተለያዩ አርአያነት ያላቸው ተግባራን በጋራ በማከናወን የመግባባትና የመቻቻል ተምሳሌት ሆነው ታይተዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ኪነ-ጥበብና ባህል ማህበር/ኪባማ/ ጎርጎራ ላይ በነበረው ፕሮግራም የወቅቱን የኢትዮጵያ ሁኔታ የሚመለከት አዝናኝና አስተማሪ ጭውውት አቅርበዋል፡፡
በደስታው ዋኘው
የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

