የአማራ ጥናት ተቋም ተቋማዊ መዋቅር አደረጃጃት መግለጫ
የአማራ ጥናት ተቋም ተጠሪነቱ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ነው፡፡ ከፕሬዚዳንቱ በመቀጠል ተቋሙን በባላደራ ቦርድ በበላይነት የሚመራው ሲሆን ባላደራ ቦርዱም ተጠሪነቱ ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ሆኖ የተቋሙን ዳይሬክተር በሃላፊነት ይመራል፣ ይቆጣጠራል፣ ያስተዳድራል፡፡ የባላደራ ቦርዱ አባላት የሚመረጡት በዩኒቨርሲቲው ፕሬዜዳንት ሲሆን የአባላቱ ስብጥርም በዩኒቨርሲቲው ውስጥ፣ ከዩኒቨርሲቲው ውጭ፣ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የሚኖሩ የተቋሙን እሴቶችና ዓላማዎች የሚደግፉና የሚያስቀጥሉ ግለሰቦች ይሆናሉ፡፡ እንደአስፈላጊነቱ ተቋማትም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የአባላቱም ብዛት ከ7 እስከ 11 ይሆናሉ፡፡
በተቋሙ ስር የሚገኙ ማዕከላት
1. የአካዳሚያዊ ፕሮግራሞች ማዕከል
ይህ ማዕከል ተጠሪነቱ ለተቋሙ ዳይሬክተር ነው፡፡ የአገራችን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአማራ ምድርንና የአማራ ህዝብን ጉዳዮችን በተመለከተ አሁን ስልጠናዎችን እየሰጡበት ካለው በተለየ እና በሰፋ መልኩ በትብብር ስልጠናዎችን የሚሰጥ ማዕከል ሲሆን ዘመኑን የዋጁ አዳዲስ ስርዓተ ትምህርቶችን በመቅረፅ እና ከጊዜ እድገት ጋር አብሮ የሚመጡ ተለዋዋጭ ጉዳዮች በአንክሮ በማጤን የአማራ ህዝብ ከራሱ አልፎ ለአገራችን እና ለዓለማችን ያበረከተውን አስተዋፅኦ በከፍተኛ ትኩረት እና በስፋት የሚመረምርና የሚያጠና ለጥቅም የሚያውል ማዕከል ነው፡፡
ማዕከሉ በአማራ ህዝብ ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ ትምህርት ክፍሎችና ተቋማት ጋር በመተባበር ስልጠናዎችን እና ፕሮግራሞችን አዘጋጅቶ በሰርተፊኬት፣ በዲፕሎማ፣ በመጀመሪያ ዲግሪና በድህረ ምረቃ ደረጃዎች ከየትኛውም የዓለም ክፍል ለመጣ ደንበኛ በሙሉ ይሰጣል፡፡
2. የጥናትና ምርምር ማዕከል
ይህ ማዕከል ተጠሪነቱ ለተቋሙ ዳይሬክተር ሲሆን ማዕከሉ የአማራ ህዝብ ባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋ እና ሌሎች አያሌ አገር በቀል ጉዳዮችን ለማጥናት፣ ሰንዶ ለማቆየትና ጥቅም ላይ ለማዋል የጥናትና ምርምር ተግባራትን በልዩነት ያከናውናል፡፡
በአማራ ህዝብ ጉዳዮች ላይ ከየትኛውም የዓለማችን ክፍል የሚመጡ ተመራማሪዎችና አጥኝዎች፣ ፖሊሲ አውጭዎች፣ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የልማት ወኪሎች እንዲሁም ሌሎች በአማራ ህዝብ ጉዳዮች ላይ ለማጥናት ቢፈልጉ የተደራጀ እና ተደራሽ የሆነ የጥናት እና ሌሎች ተዛማጅ ጹሑፎች ተደራጅተው የሚገኙበት ማዕከል ነው፡፡ ይህ ማዕከልም በአጋርነትና በትብብር ጥናትና ምርምር ያከናውናል፡፡
3. የህትመትና ጆርናል ማዕከል
የዚህም ማዕከል ተጠሪነቱ ለተቋሙ ዳይሬክተር ሲሆን የአማራ ሕዝብ ጉዳዮችን ዋና ትኩረታቸው ያደረጉ የትኛውንም አይነት አካዳሚያዊም ይሁን ከአካዳሚያዊ ውጭ የሆኑ ጹሑፎችን በመልክ በመልኩ በማደራጀት ለዓለም ተደራሽ በማድረግ የአማራን ምድርና ሕዝብ ህልውና ተጠብቆ እንዲቆይ የሚደርጉ የጥናትና ምርምር ውጤቶቸን ማሳተም ዋና ተግባሩ ሲሆን በሂደትም ራሱን የቻለ ታዋቂ ትምህርታዊ መጽሔት/ጆርናል ይመሰርታል፡፡
ይህ ማዕከል በአማራ ምድርና ህዝብ ዙሪያ የሚያተኩሩ የተዛነፉ እና የተሳሳቱ መረጃዎችን የሚያስተላልፉ ሁሉንም ዓይነት የህትመት ውጤቶችን በመለየት የማስተካከያ ግብረ መልስ የሚሆኑ ጥናቶችን ያደራጃል፡፡
4. የባህል፣ የህዝብ ግንኙነት እና ሁነት ዝግጅት ማዕከል
ይህ ማዕከል ተጠሪነቱ ለተቋሙ ዳይሬክተር ነው፡፡ ማዕከሉ የተቋሙን የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን የሚሰራ ማዕከል ነው፡፡ በተጨማሪም የአማራን ህዝብ ኪነጥበብ፣ ሙዚቃ፣ ውዝዋዜ፣ ቲያትር እና ሲኒማ የሚታይበት መድረክና ይህንን መድረክም የሚያስተባብር፣ የሚያደራጅና የሚመራ ማዕከል ነው፡፡
ከዚህም ባሻገር ተቋሙ የሚያሰናዳቸውን የተለያዩ ሁነቶንን በኃላፊነት ይመራል፤ ይከውናል፡፡
5. የቤተ-መጽሐፍት፣ የቤተ-መዛገብት እና የቤተ-መዘክር ማዕከል
ይህ ማዕከል ተጠሪነቱ ለተቋሙ ዳይሬክተር ነው፡፡ የአማራና የአማራ ህዝብ ጉዳዮችን የሚያወሱ ቤተ-መጻህፍትና ቤተ-መዛግብት በማቋቋም መጻህፍቶችን፣ መጽሔቶችን፣ ጥንታዊ ጹሑፎችን እና ሌሎች የህትመት ውጤቶች በአግባቡ ተጠብቀው ለመጭው ትውልድ ለማቆየትና የህዝብን የንባብ ባህል ለማሳደግና ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል፡፡
በተጨማሪም ማዕከሉ ሙዚየም የሚያቋቁም ሲሆን ሙዚየሙ ለተመራማሪዎች የመረጃ ምንጭ፣ ለተከታታይ አዲስ ትውልዶች የማንነታቸው መመልከቻ፣ የባህልና የታሪካቸው መማሪያና ማስረጃ ትምህርት ቤት ይሆናል፡፡
የአማራ ጥናት ተቋም ተቋማዊ መዋቅር አደረጃጃት
- Home
- የአማራ ጥናት ተቋም ተቋማዊ መዋቅር አደረጃጃት

