የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጠ
“Essential Electronic for Agriculture Library and Access to Global Online Research in Agriculture” በሚል ርዕስ ከጥቅምት 10-12/2008 ዓ.ም ድረስ በአፄ ቴዎድሮስ ግቢ ቤተ-መጽሀፍት የአሰልጣኞች ስልጠና ተካሄደ፡፡
ስልጠናዉ የተዘጋጀዉ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቤተ መጽሀፍትና ዶክመንቴሽን አገልግሎት፣ የግብርናና ገጠር ትራንስፎርሜሽን ኮሌጅ እና አሜሪካን ሃገር በሚገኝ Cornell ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ በመሆን ሲሆን፤ ከዩኒቨርሲቲያችን የግብርናና ገጠር ትራንስፎርሜሽን ኮሌጅ፣ ከቤተ-መጽሀፍትና ዶክመንቴሽን፣ከተለያዩ የትምህርት ክፍሎችና ከግብርና መምሪያ፣ ከአካባቢ ጥበቃና መሬት አስተዳደር መምሪያ፣ ከኑሮ ማሻሻያና ዘላቂ ተፈጥሮ ሀብት ፕሮግራም፣ ከአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ፣ ከጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል እና ከሌሎችም በርካታ ተቋማት የመጡ ባለሙያዎች በስልጠናዉ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ይህንን የአሰልጣኞች ስልጠና የሰጡት አቶ ተክለሚካኤል ወርዶፋ ከ ITOCA (Information training & outreach Center for Africa) የመጡ ባለሙያ ሲሆኑ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንትና የፕሬዚዳት ተወካይ የሆኑት ዶ/ር ታከለ ታደሰ ስልጠናዉን በንግግር ከፍተዋል፡፡
ዶ/ር ታከለ በንግግራቸዉም ዩኒቨርሲቲዉ በመማር ማስተማር፣ በምርምር፣በማህበረሰብ አገልግሎት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር በርካታ አመርቂ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ካሉ በኋላ፤ የዚህ ስልጠና መዘጋጀት የተጀመሩ መልካም ተግባራትን ለማቀላጠፍ እና ተደራሽ ለማድረግ ይረዳል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ተሳታፊዎች በስልጠና ላይ

በኮምፒተር የታገዘ ስልጠና ሲሰጥ
ስልጠናዉ ጥራት ያለዉ ምርምር ስራ ለመስራት፣ ጥራት ያለዉና የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር፣ የተሻለ የማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት እንዲያስችል እና በአጠቃላይ የ2ኛዉ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ለማሳካት የሚያስችል አቅምን የሚገነባ መሆኑን የቤተ-መጽሀፍትና ዶክመንቴሽን አገልግሎት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ጌታነህ ገብረሃና ገልፀዋል፡፡
አቶ ጌታነህ አያይዘዉም ይህ የአሰልጣኞች ስልጠና የተካሄደዉ በአጋር አካላት ድጋፍ መሆኑን አስታዉሰዉ ከስልጠናዉ አስፈላጊነትና ወቅታዊነት አንፃርም በቀጣይ በዩኒቨርሲቲዉ በጀት ለማስኬድ በዕቅድ መያዙን ገለጸዉ ሰልጣኞች ያገኙትን ዕዉቀት ለሌሎች በማካፈል ወደ ተግባር በመቀየር ለበለጠ ለዉጥ ጠንከረን መስራት ይኖርብናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

