የአትክልት ምርትን ለማሳደግ ጥናትና ምርምር እየተሰራ ነው
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ በድንች ዘር ላይ ምርምር እያካሄደ ይገኛል፡፡
ምርምሩ የሚካሄድበት ማዕከል በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ መቶ ሄክታር በሚሸፈን የአርሶአደሮች ማሳ ላይ ነው፡፡
የምርምር ማዕከሉ በግበርና እና ገጠር ትራንስፎርሜሽን ኮሌጅ የሆርቲ ካልቸር ትምህርት ክፍል ነው፡፡
የድንች ዘር ምርትን ከፍ ለማድረግ ከመኸር ምርት በተጨማሪ መስኖ መጠቀም አስፈላጊ በመሆኑ ለአካባቢው ተሰማሚ የሆኑ 13 የድንች ዘሮችን በማሰባሰብና በመምረጥ ለአርሶአደሮች እያከፋፈልን እንገኛለን በማለት የማዕከሉ ኃላፊና የማህበረሰብ አገልግሎት ተወካይ አስተባባሪ አቶ ሰለሞን ፈንታሁን ገልጸዋል ፡፡
[widgetkit id=7688]
በተጨማሪም ምን አይነት ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግና በአካባቢው የመስኖ ውሃ አጠቃቀም ችግር በመኖሩ ምን ያህል የውሃ መጠን መጠቀም እደሚያስፈልግ ጥናትና ምርምር ጎን ለጎን እየተሰራ መሆኑንም አያይዘው ገልፀዋል፡፡ እስካሁን በስፋት ጥቅም ላይ ከዋሉት የድንች ዘር ”በለጠ” በሚል ስያሜ የሚጠራው የድንች ዘር ውጤታማ ሆኖ የማህበረሰቡን ችግር እየፈታ የሚገኝ መሆኑን አስተባባሪው አክለው ገልፀዋል ፡፡
የድንች ዘር ማባዣ ማዕከሉ ለበርካታ አርሶ አደሮችና ወጣቶች ዘርን በማከፋፈልና በአመራረቱ ላይ ችግር እንዳይፈጠር ድጋፍ በማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡ በድንች ዘር ምርምር ማዕከሉ ተጠቃሚ ከሆኑት አርሶአደሮች ውስጥ አርሶአደር ተፈራ ነጋሽ እና አርሶአደር አዳነ አለሙ ከወቅን ዙሪያ ቀበሌ ናቸው፡፡አ/አደሮቹ እደገለፁት እያንዳንዳቸው 6 ኩንታል የድንች ዘር ተረክበው 60 ኩንታል ምርት ለገቢያ የሚቀርብና 15 ኩንታል ለቤት ፍጆታ የሚውል በድምሩ 75 ኩንታል የድንች ዘር ምርት ያመረቱ ሲሆን 30 ሸህ ብር ገቢ ማግኝታቸውንም ጭምር ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ውጤት እንዲበቁ የረዳቸው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመሆኑ የምርምር ስራውና ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና ሁሉም አርሶአደሮች የምርቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መልክታቸውን አስተላለፈዋል፡፡
በድንች ዘር ምርምር ማዕከሉ ህዳር 14/2010 ዓ.ም ጉብኝት የተደረገ ሲሆን የጎንደር ዩኒቨርሰቲ አመራር አካላት፣ የአካባቢው አርሶአደሮች፣ የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅትና የኢትዮጵያጊ ዜና አገልግሎት ጎንደር ቅርንጫፍ ጋዜጠኞች ተገኝተዋል፡፡ በጉብኝቱ ወቅት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ህበረተሰብ አገልግሉት ም/ፕሬዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ ምርምሩ የተሰራው ከአርሶአደሮች ማሳ ላይ ከመሆኑ ባሻገር አርሶአደሮቹ ከሚጠበቀው በላይ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡ እስካሁን የሚመረተው የድንች ዘር ከመቶ ኩንታል የማይበልጥ በመሆኑ ቀጣይ የዚህን 5 እጥፍ ለማምረት በእቅድ እየተሰራ መሆኑንም አክለው ገልፀዋል ፡፡
ዘጋቢ ፡ – በላይ መስፍን
ሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬትት

