የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታን የሚያሻሽሉ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የእንግሊዝኛ ቋንቋና ስነ-ፅሁፍ ትምህርት ክፍል የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ ማዕከል በነፃ ሀሳብን የመግለፅ (free talk) ክለብ አባላት ሳምንታዊ (ፍሪ ቶክ) ፕሮግራማቸውን ጥር 18/2010 ዓ/ም በማዕከሉ ክፍል አካሄዱ፡፡
ዩኒቨርሲቲዎች የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ ማዕከል እንዲከፍቱ በትምህርት ሚኒስቴር በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት የጎንደር ዩኒቨርሲቲም ከ2009 ዓ/ም ጀምሮ ማዕከሉን በመክፈት የተማሪዎችን ፣ የመምህራንንና የአስተዳደር ሰራተኞችን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎታቸውን ለማዳበር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል :: በመሆኑም ባለፈው ዓመት ለኮሌጁ ተመራቂ ተማሪዎች በሲቪ አፃፃፍና በምስለ ቃለ-መጠየቅ፣ በአሁኑ ዓመት ደግሞ ከ200 በላይ ለሆኑ ለአዲስ ተማሪዎች በደሊቨሮሎጂ ፅንሰ ሀሳብ ዙሪያና በመሳሰሉት ስልጠና ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ለዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ትምህርት ቤት /Community School/ ለእንግሊዝኛ መምህራን የማስተማር ዘዴ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
[widgetkit id=8195]
ከዚህም በተጨማሪ ለተማሪዎች በዳሰሳ ጥናት ላይ የተመሰረተ የአጭር ጊዜና የመካከለኛ ጊዜ ስልጠና በመስጠት ላይ ነው፡፡እንዲሁም የተለያዩ ክበባትን በማዋቀርና ተማሪዎቹ እንዲሳተፉ በማድረግ ፣ማዕከሉ ለቋንቋው ማሻሻያ በሚያግዙ በተለያዩ መጽሄቶች ፣ጋዜጣዎች፣ ቪዲዮዎችና በመሳሰሉ ቁሳቁሶች በማሟላት፣ የቱቶሪያል ትምህርት በመስጠት በተጨማሪም ሁነቶችን በማመቻቸት ተማሪዎች በማንኛውም ሰአት ማዕከሉን በመጠቀም የቋንቋ ክህሎታቸውን እንዲያሻሽሉ እንዳገዛቸው የማዕከሉ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ምስጋናው ጥላሁን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም መምህራንን በንባብ ክለብ በማሳተፍ በየ15 ቀኑ ሀሙስ የተለያዩ አጫጭር ልቦለዶችን /Short Stories/ እንዲያነቡና በነሱ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ የመምህራንን አቅም በማጎልበት የተሳለጠ መማር ማስተማር እንዲኖር አየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡
(የፍሪ ቶክ) ክለብ አባላትም አርብ ሳምንታዊ ፕሮግራም ያላቸው ሲሆን ጥር 18/2010 ዓ/ም በነበረው ዝግጅት ላይ ተገኝተን አባላት በነፃ ሀሳባቸውን ሲገልፁና በስፋት ሲወያዩ ተከታትለን ሀሳባቸውን እንዲያካፍሉንም አድርገናል፡፡እነዚህም የክለቡ አባላት ከተለያዩ የትምህርት ክፍሎች የመጡ ሲሆኑ፣ ተማሪ ዘውዴ ጌታነህ ፣ ማህሌት አየለና አስቴር ታፈሰ እንደገለፁት፣ በክለቡ መሳተፋቸው የቋንቋ ክህሎታቸውን ለማሻሻል እንደረዳቸው ፣ የተሻለ የቋንቋ ችሎታና ፍላጎት እንዳሳደረባቸውና በራስ የመተማመን ስሜት እንደፈጠረላቸው ገልፀዋል ፡፡
ወደፊትም ለአስተዳደር ሰራተኞች በተለይም ለፀሀፊዎች ፣ ለዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ትምህርት ቤት መምህራንም 2ኛ ዙር ስልጠና እንደሚሰጥና በአሁኑ ሰአት በማራኪ ግቢ ብቻ እየተሰራ ያለውን ስራ በሌሎች የዩኒቨርሲቲው ግቢዎች የማስፋፋት ስራ እንደሚሰራ አቶ ምስጋናው ገልፀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- የሽመቤት ኃይሉ
ኤዲተር፡- ይዳኙ ማንደፍሮ