የወጣቶች ኢንተርፕራይዞችን ማበረታታት ፋይዳው የጎላ ነው፡፡
ወጣቶችን በማህበራት ማደራጀት የወጣቶችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ሆነ ስራ አጥነትን በመቀነስ ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ይታመንበታል፤ ስለሆነም አንዳንድ ስራ ፈላጊ ወጣቶችን በተለያዩ ማህበራት በማደራጀትና ውጤታማ በማድረግ ለራሳቸውና ለአካባባቢያቸው ብሎም ለሀገራቸው ትርጉም ያለው ስራ እንዲሰሩ በማስቻል ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ ተደርጓል፡፡ በተቃራኒው በማህበራት ከተደራጁ በኋላ እዚህ ግባ የሚባል ውጤት ያላሳዩ፣ ባሉበት የሚድሁ ብሎም ድራሻቸው የጠፉ ማህበራትን በየአካባቢያችን መመልከት የተለመደ ነው፡፡
በሜ.ቴ.ክ እገዛ በ2007 ዓ.ም ለ100 ስራ ፈላጊ ወጣቶች እንደተቋቋመ የሚነገርለት ጎንደር አዘዞ የሚገኘው የቴወድሮስ፣ የገብርየ፣ የፋሲልና ጓደኞቹ ፍሌክሴብል ብረታብርት ኢንጅነሪንግ ወርክ ሾፕ በአሁኑ ሰአት 76(50 ወንድና 26 ሴት) አባላት አሉት፡፡ ማህበሩ የመበተን እጣ እንዳይገጥመው ለመታደግ ይቻል ዘንድ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በፊት የፋይናንስ/200,000 ብር/ እና የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጉ ይታወሳል፡፡ አሁን ደግሞ በዩኒቨርሲቲው አሰተባባሪነት ከሚመለከታቸው ከክልል፣ ከዞንና ወረዳ ባለድርሻ አካላት ጋር የዩኒቨርሲቲው የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ በተገኙበት ሚያዚያ 11/2010 ዓ.ም ውይይት ተደርጓል፡፡
[widgetkit id=8969]
የውይይቱ አላማ ማህበሩ ያሉበትን ችግሮች በመቅረፍና ውጤታማ በማድረግ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማስቻል እንደሆነ የገለጹት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን መስፍን ናቸው፡፡ አቶ ሰሎሞን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው አያይዘው እንደተናገሩት የወጣቶች ኢንትርፕራይዞችን በማንኛውም መልኩ መደገፍ/ማገዝ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት በመሆኑ መሰል ውይይቶች ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
መንግስት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር እንዲሸጋገር ለማድረግ ከሚንቀሳቀስባቸው መንገዶች አንዱ የማንፋክቸሪንግ ዘርፍ ነው ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ ንግድ ኢንዱስትሪ ገብያ ልማት መምሪያ ም/ኃላፊ አቶ አስፋው ገ/እግዚአብሔር ናቸው፡፡ በክልሉ ስራ ፈላጊ ወጣቶችን በተለያዩ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በማደራጀት ወደ ስራ እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ አወንታዊ ለውጦች መታየታቸውን አቶ አስፋው በመክፈቻ ንግግራቸው ገልጸዋል፡፡ አቶ አስፋው አያይዘውም የቴወድሮስ፣ የገብርየ፣ የፋሲልና ጓደኞቹ ፍሌክሴብል ብረታብርት ኢንጅነሪንግ ወርክ ሾፕ አስተዳደራዊ ክፍተቶችና የገቢያ ትስስር እጥሮቶች እንዳሉበት ገልጸው ለወደፊቱ ማህበሩ እንዲጣናከር የበኩላቸውን ድርሻ በቢሯቸው በኩል እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል፡፡
ስለማህበሩ አጠቃላይ የስራ ክንውን፣ ችግሮችና ለወደፊት ምን አይነት እገዛ እንደሚያስፈልግ በማህበሩ የገቢያ ትስስር ም/ኃላፊ በአቶ ወርቁ አናጋው የቀረበውን ሪፖርት መሰረት በማድርግ ሰፊ ውይይት በተሳታፊዎች ተደርጓል፡፡ ወርክ ሾፑም በተሳታፊዎች በአካል ተጎብኝቷል፡፡ የገብያ ትስስር አለመኖር ፣ በቂ የግብዓት አቅርቦት አለመኖርና አባላት በቂ ስልጠና አለማግኘታቸው በተሳታፊዎች በስፋት ከተጠቀሱ ችግሮች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ለወደፊትም በተጠቀሱት ችግሮችና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በስፋት መሰራት እንዳለበት በመስማማት ውይይቱ ተጠናቋል፡፡
ዘገባ፡ አምሳሉ ግዛቸው

