የዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ 150ኛ የሙት አመት መታሰቢያ በተለያዩ ዝግጅቶች ሊከበር ነው
በኢትዮጵያውን ዘንድ ከጊዜያቸው ቀድመው የተወለዱ መሪ በመባል የሚጠቀሱት ዳግማዊ አፄ ቴወድሮስ በትውልድ ስማቸው ካሳ ኃይሉ፣ በፈረስ ስማቸው አባ ታጠቅ፣ በወታደራዊ ስማቸው መይሳው ካሳ እንዲሁም አንድ ለእናቱበመባል የሚታወቁት አጼ ቴዎድሮስ የዘመናዊ ስልጣኔ በር ከፋችና አንድ የሆነች የጠንካራ ኢትዮጵያ ምልክት መሆናቸውን የተለያዩ የመረጃ ምንጮች ይገልፃሉ፡፡(wikipedia)
[widgetkit id=7242]
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል አነሳሽነት ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ ትልቅ ራዕይ የነበራቸውን የዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ 150ኛ የሙት አመትን ምክንያት በማድረግ “መቅደላ 150” በሚል መሪ ቃል የንጉሱን አስተዳደግ፣ ርዕይና አሟሟት፣ ለኢትጵያ አንድነት፣ ዘመናዊነትና የዕውውት ሽግግር ያመጡተን ለውጥ የሚዘክር ዝግጅቶች ሊካሄድ ነው፡፡ የዚህ ዝግጅት ዋና አላማም አጼ ቴዎድሮስ ትተዋቸው ያለፉ ነገሮችን በማስታወስና ከእሳቸው ህይወት ወጣቱ እንዲማር ብሎም እሳቸው ጀምረዋቸው ያለፏቸውን ነገሮችና ራዕያቸውን ተቀብሎ ፍፃሜ ላይ ለማድረስና ለማነሳሳት የታሰበ ፕሮግራም መሆኑን የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ የማርሸት ግርማይ ተናግረዋል፡፡
በዚህ የመታሰቢያ ዝግጅት ላይ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሚሳተፉ ሲሆን፣ ዝግጅቱም በአጼ ቴዎድሮስ ላይ የተፃፉ መፃህፍትንና ጥናትና ምርምሮች በማሰባሰብ ለኤግዚቢሽን በማቅረብ፣ አፄ ቴዎድሮስ ወደ ተወለዱበት ፣ወደ አደጉበት፣ ወደ ነገሱበት፣ የፖለቲካ መቀመጫ ወዳደረጉትና በተለይ ደግሞ ቴክኖሎጅ ላይ ብዙ ስራ ወደ ሰሩበት ወደ ደብረታቦርና ጋፋት በመጨረሻም ህይወታቸው ወዳለፈበት ወደ መቅደላ በሚደረጉ ጉዞዎችና በነዚህ ቦታዎችም በሚደረጉ የፓናል ውይይቶ፣ ጉብኝቶች፣ ፌስቲቫሎችና ሌሎች ጉዳዮችን በማከናወን በዓሉ ይታሰባል፡፡ በመጨረሻም ለዚህ ዝግጅት አሻራ ሊሆን የሚችል ስራ እንደሚሰራ ለምሳሌ ሀውልታቸውን ለማቆም የመሰረት ድንጋይ የመጣል ወይም ሙዚየም ለመገንባት ወይም በስማቸው ፋውንዴሽን ለማቋቋም መታሰቡን አቶ ማርሽት ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ይህን ዝግጅት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሲያስተባብር የባሀር ዳር፣ የደብረታቦርና የመቅደላ ዩኒቨርሲቲዎችም በጋራ እንደሚሰሩ እና ለዚህም በየበኩላቸው የሚያከናውኗቸው ተግባራት ተሰጥቷቸው እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ይህ ዝግጅት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ በሚመራና የጎንደር ከተማ ከንቲባ እንዲሁም የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ የተካተቱበት የበላይ ጠባቂ ሲኖረው፣ ዝግጅቱን በተለያዩ ተግባራተ የሚያንቀሳቅሱ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ባለሀብቶችና የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ማህበርን በአባልነት ያካተተ 9 ያህል ኮሚቴዎች ተዋቅረዋል፡፡ ኮሚቴዎችም በተሰጣቸው የስራ ዝርዝር ላይ ለመወያየትና የመፈፀሚያ እቅዳቸውን ለማውጣት ህዳር 6/2010 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው የHDP አዳራሽ የመጀመሪያ ውይይታቸውን አካሂደዋል፡፡
አጼ ቴዎድሮስ ትልቅ ስራ የሰሩና ባለራዕይ መሪ የነበሩ በመሆኑ የሚዘጋጀው ዝግጅት የእሳቸውን ስም የሚመጥን ለማድረግ ህብረተሰቡ ከጎናቸው እንዲሆን አስተባባሪዎች መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ እኛም ለዚህ አላማ ሁሉም የበኩሉን በመወጣት ለበዓሉ ስኬት እንረባረብ እንላለን፡፡
ዘጋቢ፡ መሰረት አለምነህ
የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

