የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ 150ኛ ዓመት ዝክረ ሰማዕት በዓል እየተከበረ ነው፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ሀሳብ አመንጭነት የተጀመረው እና አማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ከአ.ብ.ክ.መ ባህልና ቱሪዝም ጋር በጋራ በመሆን ያዘጋጁት 150ኛ ዓመት ዝክረ ሰማዕት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በዓል ከዛሬ ሚያዚያ 2/2010 ዓ.ም ጀምሮ በጎንደር ኒቨርሲቲ ሳይንስ አምባ አዳራሽ እየተከበረ ነው፡፡
በበዓሉ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለን መንገሻ፣ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ተቀባ ተባባል ፣የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሒሩት ካሳው፣ የሳይንስና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር የአካዳሚክና ምርምር ጉዳዮች ጀኔራል ዳይሬክተር ዶ/ር ስሜነው ቀስቅስ፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ፕሬዚዳንቶችና ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ ከዞንና ወረዳዎች የመጡ የባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ቤተሰቦች፣ በአፄ ቴዎድሮስ ዙሪያ ጥናትና ምርምር ያደረጉ የታሪክ ተመራማሪዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የመጡ ባለሙያዎች፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ተማሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
[widgetkit id=8853]
‹‹ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ መስዋዕትነት የከፈሉበትንና የኢትዮጵያዊነት ኩራት ጥጉ የት ድረስ እንደሆን ያሳዩበትን ቀን ስንዘክር ለተራ ውዳሴ ሳይሆን ለላቀ የሀገር አንድነት፣ ፍቅር፣ መተሳሰብና በክብር መሰዋት ያለውን ፋይዳ ለትውልድ ማስተላለፍ የሚያመጣውን ሀገራዊ ጠቀሜታ በመረዳት ነው፡፡” ብለዋል፡፡ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ተቀባ ተባባል በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው፡፡ በዓሉን በንግግር የከፈቱት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለን መንገሻ በበኩላቸው “መቅደላ ላይ የተዘረፉ የማንነታችን መገለጫ የሆኑ ቅርሶቻችን ለማስመለስ፣ ሙዚየሞችን ለማቋቋም፣ ሀውልቶችን ለማቆምና መንገዶችን ለመዘርጋት መተባበር ይኖርብናል” ብለዋል፡፡
በመርሀ ግብሩ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሒሩት ካሳው እና ታዋቂው የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ቁልፍ ንግግር አቅርበዋል፡፡ በንግግራቸውም የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ እሴቶች ምን ምን ናቸው የሚለውንና ዘመን የማያደበዝዘው የአፄው አሻራዎች ተዳስሰዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል መምህር በሆኑት አቶ አበባው አያሌው የቀረበው የመወያያ ጥናታዊ ፅሁፍም ‹‹ የጀግኖች ሽሚያ ወደ……›› የሚል ርዕስ ሲኖረው፣ ሰፊ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡ከጥናታዊ ጽሁፎች በተጨማሪ አፄ ቴዎድሮ የፃፏቸው የተለያዩ ደብዳቤዎች፣ ፎቶዎች፣ የልጃቸው የአለማየሁ ቴዎድሮስ ፎቶዎች፣ ስለ አፄ ቴዎድሮስ በተለያዩ ፀሀፊዎች የተፃፉ ታሪኮች ወዘተ፣ የያዘ አውደ-ርዕይ ዝግጅት በማድረግ የበዓሉ ታዳሚዎች ጉብኝት አካሂደዋል፡፡
በዚህ የ150ኛ ዓመት ዝክረ ሰማዕት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በዓል አከባበር በአፄው ሰብዕና፣ በመቅደላ ወታደራዊ ሁኔታዎችና በተዘረፉ ቅርሶች ላይ ያተኮሩ ከ30 በላይ ጥናታዊ ፅሁፎች ይቀርባሉ፡፡ በዓሉም በጎንደር፣ በደብረታቦር፣ በመቅደላ አምባና በአዲስ አበባ በተለያዩ ዝግጅቶች እስከ ሚያዚያ 8/2010 ዓ.ም ይከበራል፡፡

