የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለአዲስ መምህራን ስልጠና ሰጠ

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራት ማረጋገጫ እና ኦዲት ዳይሬክቶሬት የመማር ማስተማር ሂደቱን አስመልክቶ በጎንደር ከተማ ታዬ በላይ ሆቴል ከጥቅምት 20 እስከ 21/2008 ዓ.ም ድረስ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
ስልጠናዉን በይፋ የከፈቱት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት እና የዩኒቨርሲቲዉ ተወካይ ፕሬዚዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ እንደተናገሩት የዛሬዉን የአዲስ መምህራን ስልጠና ከዚህ ቀደም ከተሰጡት ስልጠናዎች ለየት የሚያደርገዉ ዩኒቨርሰቲያችን መቀሌ በተካሄደዉ 25ኛዉ የትምህርትና ስልጠና ጉባኤ የዋንጫ ተሸላሚ በሆንበት ማግስት ላይ በመሆኑ አዲስ ለተቀጠራችሁ መምህራን ወደፊት ለበለጠ ስኬት እንድትተጉ የሚገፋፋ ነዉ ብለዋል፡፡ ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ አያይዘዉም መምህራኑ በምርምር፣ በማህበረሰብ አገልግሎት፣ በትምህርት ጥራት፣ በመልካም አስተዳደር እና ሙስናን በመዋጋት ኃላፊነትን መወጣት እንደሚገባቸዉ በመግቢያ ንግግራቸዉ ላይ ገልፀዋል፡፡
የስልጠናዉ ዓላማም በአጠቃላይ በዩኒቨርሲቲዉ የሚከናወኑ ተግባራትን ለማስተዋወቅ እና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እንደሆነ የትምህርት ጥራት ማረጋገጫና ኦዲት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር የማታዉ ወንዴ ለሰልጣኝ መምህራኑ በሰጡት ገለፃ መረዳት ተችሏል፡፡

ስልጠናዉ በቀለም ትምህርት አተገባበር ስርዓት፣ በትምህርት ዕቅድ፣ በአሳታፊ የትምህርት ዘዴ፣ በማማከር አገልግሎት፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት፣ በትምህርት ጥራትና ማረጋገጫ ዘዴ፣ በ5 ዓመቱ የዕድገትና ሽግግር ዕቅድ፣ በኃላፊነት ግዴታዎች፣ በልዩ ፍላጎትና ኤች አይ ቪ ኤድስ፣ በእነዚህ አስር ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በተቀመጠላቸዉ ጊዜ ገደብ ገለፃ ከተካሄደባቸዉ በኋላ ሰልጣኞቹ ጥያቄዎችን እያነሱ ሰፊ ዉይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡
ዉይይቱን አስመልክቶ ከሰልጣኝ መምህራኑ መካከል ያነጋገርናቸዉ ስልጠናዉ አጠቃላይ ስለ ዩኒቨርሲቲዉ ግንዛቤ የፈጠረላቸዉ መሆኑን እና ወደ ስራ ሲገቡ እንደማይቸገሩ የገለፁ ሲሆን ወደፊትም ስልጠናዉ መቀጠል እንዳለበት በአስተያየታቸዉ አስቀምጠዋል፡፡
በመጨረሻም ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ ከግል ህይወታቸዉ በመነሳት አጠቃላይ የዩኒቨርሲቲዉን ተሞክሮ ለሰልጣኞች ገልፀዉ የዕለቱን ፕሮግራም በመዝጊያ ንግግራቸዉ ቋጭተዋል፡፡


