የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ጊዜያዊ ማረፊ
የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ የተመሰረተው በ1960 ዓ.ም ሲሆን በውቅቱ አብረው የተመሰረቱ እንደ ኒያላ፣አስመራ መንገድ፣ፔፕሲ፣ ኢዲዲሲና መከላከያ ያሉ የ እግር ኳስ ክለቦች ከጊዜ ወደጊዜ እየከሰሙ መምጣተቸውን የከተማው ነዋሮዎች ይናገራሉ ፡፡ በአንጻሩ የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ተስፋን በሰነቁ ደጋፊዎቹና ተጫዋቾቹ አሁን ከደረሰበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ አስችሎታል ይላሉ ነዋሪዎቹ፡፡የክለቡ ደጋፊ ማህበር ጽ/ቤት በበኩሉ ክለቡን ወደተሸለ ደረጃ ለማሸጋገር በየጊዜው በሚያቀርባቸው የድጋፍ ጥያቄዎች በርካታ ደጋፊዎችን ማፍራት ችሏል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲም በ2009 ዓ.ም ለክለቡ ማጠናከሪያ የሚሆን የ4ሚሊዮን ብርና የትጥቅ ድጋፍ ያደረገና እያደረገ ያለ ነው፡፡ ክለቡ አሁንም የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን የተሟላ ካፌና ሬስቶራንት ያለውን የዩኒቨርሲቲውን እንግዳ ማረፊያ በጊዜያዊነት ለክለቡ አገልግሎት እንዲውል የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት በወሰነው መሰረት መስከረም 25/2010 ዓ.ም የክለቡ አባላትና ደጋፊዎች በተገኙበት በይፋ ተበስሯል፡፡
በአቀባበሉ ላይ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ባደረጉት ንግግር ባለፉት ጊዜያት የተለያዩ ክለቦች በከተማችን የነበሩ ቢሆንም ድጋፍ በማጣታቸው ምክንያት ወደኋላ ቀርተዋል፡፡ ተስፋ ያልቆረጠው አንጋፋው የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ በፕሪሜር ሊግ ደረጃ የመጫወት አቅሙን ያሳደገ ሲሆን እንደ ዩኒቨርሲቲ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ድጋፍ እያደረግን እንገኛለንˮ ብለዋል፡፡
ዶ/ር ደሳለኝ አያይዘውም የክለቡ ማረፊያ የነበረው ቦታ በግንባታ ምክንያት በመነሳቱ የዩኒቨርሲቲው እንግዳ ማረፊያ ሆቴል በጊዜያዊነት ለክለቡ መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በፊት ያርፉበት ከነበረው ቦታ በተሻለ የምኝታ፣የሬስቶራንትና የኢንተርኔት አገልገሎት በመኖሩ ተጫዋቾች የተሸለ ዕረፍት ማግኘት የሚችሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ክለቡ እያደገ በመምጣቱ ጊዜያቸውን በአልባሌ ቦታ ያሳልፉ የነበሩ በርካታ ወጣቶች ክለቡን በመደገፍ ራሳቸውን መጠበቅ እንዲችሉ ረድቷቸዋል ነው ያሉት ዶ/ር ደሳለኝ እንደዚህ ዓይነቱን ክለብ መደገፍ ማህበረሰብን መደገፍ ስለሆነ በቀጣይም ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን በማለት ንግግራቸውን ቋጭተዋል፡፡
የፋሲል እግር ኳስ ክለብ ደጋፊ ማህበር ምክትል ሰበሳቢ አቶ ሀብቱ ሰፊው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማረፊያ ቦታ ድጋፍ ባያደርግላቸው ኖሮ ችግር ውስጥ እንደሚሆኑ እና ከዚህ በፊት የነበረው ቦታ ምቹ ባለመሆኑ ተጫዋቾች በየሆቴሉ ያድሩ እንደነበረም ገልጸዋል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ላደረገላቸው ድጋፍም ከፍ ያለ ምስጋናን አቅረበዋል፡፡
ከሌሎች የደጋፊ ማህበሩ አባላት እንደተገለጸው የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ እጥረት በነበረበት ጊዜ በከተማው ተፅኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን በማሰባሰብ ክለቡ እንዴትና በምን መደገፍ እንዳለበት የተለያዩ ሐሳቦችን በማፍለቅ ድጋፍ ጠይቆ ማግኘት የማይችል የነበረው ፋሲል ከነማ ዛሬ በተለያዩ ድርጅቶች ተጠይቆ ድጋፍ ማግኘት የሚችልበት እድል ተፈጥሯል ፡፡
ከ4 ዓመታት በፊት 1.5 ሚሊዮን ብር ካፒታል የነበረው ፋሲል ከነማ በአሁኑ ሰዓት 50 ሚሊዮን ብር ካፒታል መደረሱንም ከማህበሩ አባላት መረዳት ችለናል፡፡
ዘጋቢ፡-በላይ መስፍን
ኤዲተር፡-ደምሴ ደስታ
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

