የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርማቲክስ ፋካሊቲ ኢንፎርሜሽን ሲስተምስ ት/ክፍል ሀገራዊ የሆነ ወርክ ሾፕ አካሄደ፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርሜሽን ሲስተምስ ት/ክፍል “The Role and Position of Information Systems in the Computing Landscape” በሚል ርዕሰ ጉዳይ የኢንፎርሜሽን ሲስተምስ በሀገር አቀፍ ደረጃ ስላለበት ሁኔታ፣ እየተተገበረና ለወደፊት መሰራት ስላለባቸው ጥናቶች እንዲሁም ከቢዝነሱ ጋር ስላለው የጠበቀ ግንኙነት እና ተያያዥነት ስላላቸው ጉዳዮች ከሚመለከታቸው የመንግስትና የግል መስሪያቤቶች፣ ድርጅቶችና ተቋማት ጋር የካቲት 25/2009 ዓ.ም በሩት ሆቴል የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሰፊ ውይይት አድርጓል፡፡

በመጀመሪያ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርማቲክስ ፋካሊቲ ዲን አቶ ቴወድሮስ አለሙ በአቶ ወርቁ አበበ የኢንፎርሜሽን ሲስተምስ ት/ት ክፍል ሀላፊና የእለቱ ፕሮግራም አስተዋዋቂ ጋባዥነት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ አቶ ቴወድሮስ እንደ ገለጹት፣ የወርክሾፑ አላማ “ኢንፎርሜሽን ሲስተምስ”ን አሁን ካለበት ደረጃ ወደ ላቀ ሁኔታ በማሳደግ በሀገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ ድርጅቶች ሳይንሱን በአግባቡ በመጠቀም አላማቸውን ወይም ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚረዳ ከመሆኑም በላይ በያንዳንዱ እንቅስቃሴአችን ኑሯችንን ቀላል ለማድረግ የሚረዳ አይነተኛ መሳሪያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሰቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ “ወርክሾፑ”ን በንግግር ሲከፍቱ እንደተናገሩት “ኢንፎርሜሽን ሲስተምስ” ለሃገር እድገት ዋና ሚና እንደሚጫዎት የምራባዊያንን ተሞክሮ በምሳሌነት በማጣቀስ ለተሳታፊዎች አስረድተዋል፡፡ ዶ/ር ደሳለኝ በዩኒቨርሲቲው ግብዣ ተደርጎለቸው በወርክሾፑ ላይ ለመሳተፍና ያካበቱትን ከፍተኛ ልምድ ለማካፈል ከተለያዩ ተቋማት ለመጡ ሙህራን እና ወርክሾን ላዘጋጁት የት/ት ክፍሉ መምህራን እንዲሁም ለሌሎች አጋር አካላት ምስጋናቸውን ገልጸዋል፡፡

የመገናኛና የኢንፎርሜሽን ሚንስተር፣ የሚንስተሩ ቴክኒካል አማካሪ ዶ/ር መስፍን በላቸው ቁልፍ ንግግር (key note speech) አድረገዋል፡፡ በንግግራቸው ኢንፎርሜሽን ሲስተምስ ለሃገር እድገት ያለውን ጥቅም በስፋት ዳሰዋል፡፡


በመቀጠል ከተለያዩ ተቋማት በመጡ የዘርፉ ሙሁራን (በዶ/ር ጥበበ በሻህ፣ በዶ/ር አቢዎት ሲናሞ፣ በዶ/ር ሚሊየን መሸሻ፣ በዶ/ር ተምትም አሰፋ እና በአቶ ዘላለም አሰፋ) የእለቱን ርዕሰ ጉዳይ የተመለከቱ የተለያዩ ጽሁፎች ቀርበዋል፡፡ የቀረቡ ጽሁፎችን መነሻ በማድረግም ሰፊ የሆነ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ለወደፊት ይበጃሉ የተባሉ ዝክረ ሀሳቦችም በስፋት ተሰንዝረዋል፡፡

በመጨረሻም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ም/ፕረዝዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን የእለቱን ወርክ ሾፕ በንግግር ዘግተዋል፡፡ ዶ/ር አስራት ወርክሾፑን ላዘጋጀው ሊኢፎርሜሽን ሲስተምስ ት/ት ክፍል፣ ተሳትፎ ላደረጉ ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እና አጋር አካላት ያላቸውን ምስጋና ገልጸዋል፡፡ ዶ/ሩ እንዳሉት መሰል ውይይቶች ለሃገር እድገት ብሎም የዩኒቨርሲቲዎችንን አቅም ለማሳደግ የሚረዳ በመሆኑ ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው በአንክሮ ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም በመሰል ጉዳዮች ለመገናኘት ያላቸውን ጽኑ እምነት በመግለጽ የዕለቱ ውይይት ተጠናቋል፡፡
ዘጋቢ፡- አምሳሉ ጋዛቸው

