የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ምክክር አደረገ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ አካባቢ የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በተለይም የአርግን ጆና ቀበሌ ነዋሪዎችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር ህዳር 29/2010 ዓ/ም በደባርቅ ከተማ በፓርኩ ጽ/ቤት አዳራሽ ምክክር ተደረገ፡፡ በዕለቱ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ የደባርቅ ከተማ የአመራር አካላት፣ የአርግን ጆና ቀበሌ ሊቀ መንበርና ጥሪ የተደረገላቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡
[widgetkit id=7862]
ባለፈው አመት ሰኔ 9/2009 ዓ/ም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስርዓተ- ፆታና ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከታተያ ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት የተዋቀረ የጥናት ቡድን ከቦታው ድረስ ተገኝተው የቀበሌውን ማህበረሰብ የአኗኗር ሁኔታ ምን እንደሚመስል ፣ በአካባቢው ያሉ ምቹ የኢኮኖሚ አማራጮች ምን ምን እንደሆኑ? ከአምባራስ ቁጥር 2 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማህበረሰብና ከቀበሌው ነዋሪዎች ጋር ሰፊ ውይይት በማካሄድ (need assessment) በመስራት በተለያየ መንገድ መረጃ ሰብስበው መምጣታቸው ይታወሳል፡፡
ፕሮግራሙን ወ/ሮ ደብረወርቅ ይግዛው የደባርቅ ከተማ አስተዳዳሪ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገው፣ ዶ/ር ዘውዱ ተሾመ የምርምርና ህትመት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የመክፈቻ ንግግር እንዲያደርጉ ተጋብዘዋል፡፡ ዶ/ር ዘውዱም ይህ እየተሰራ ያለው ጥናትና ምርምር ዩኒቨርሲቲዎች በአዋጅ ከተቋቋሙበት አላማ አንዱ እንደሆነ አስታውሰው የሰሜን ፓርክን ደህንነት መጠበቅና የአካባቢውን ማህበረሰብ ዘላቂ በሆነ መንገድ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ያለውን ስራ በማድነቅ ዩኒቨርሲቲው እንደ ባለድርሻ አካል የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በመቀጠልም ጥናት አድራጊዎች መ/ር ተወልደ ገ/መድህን እና መ/ር የኔሰው አለነ ጥናቱን ያቀረቡ ሲሆን፣ የዳሰሳ ጥናቱን መነሻ በማድረግ በርካታ ጥያቄዎች ቀርበው በስርአተ ፆታና ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በወ/ሮ ትዕግስት ጴጥሮስ፣ በአጥኝዎቹና በተሳታፊዎች ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡በቀጣይም ህብረተሰቡ በዘላቂነት በኢኮኖሚ ተጠቃሚ በሚያደርጉ የመፍትሄ ሀሳቦች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡
በመጨረሻም ወ/ሮ ደብረወርቅ ይግዛው የደባርቅ ከተማ አስተዳዳሪ ዩኒቨርሲቲው በሁሉም መስክ እያከናወነ ያለውን ተግባር አመስግነው፣ የዚህን አካባቢ ማህበረሰብ ችግር ለመፍታት ለአንድ ወገን የሚተው ሳይሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን በመወጣት የተጠቆሙትን የመፍትሄ ሀሳቦች ለመፈፀም ጥረት ቢደረግ መልካም መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው በማሳሰብ አጠናቀዋል፡፡

