የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጪው 20 ዓመታት ፍኖተ ካርታ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጪው 20 ዓመታት የምድረ ግቢ ዲዛይን መሪ ዕቅድ/master plan የመጀመሪያ ዙር የንድፍ ስራ ግምገማ ከባለድርሻ አካላት ጋር በተለያዩ ውይይቶች፣ የግቢ ምልከታዎች እና ገለጻዎች ህዳር 26-27/2010 ዓ.ም በዩኒቨርሲው ግቢ ተካሂዷል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በፊት የነበረውን ዘልማዳዊ የግንባታ ቦታ አጠቃቀም ሳይንሳዊ ሂደቱን በጠበቀና ለሌሎች ተቋማትና ከተሞች ተምሳሌት እንዲሆን የሚያግዝና እና ተቋሙ ለጎንደር ከተማ ገጽታ አወንታዊ ሚና እንዲኖረው በሚያስችል ሁኔታ የ20 ዓመት የምድረ ግቢ ዲዛይን መሪ ዕቅድ ለመተግበር ቅድመ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ ተቋሙ ከኢትዮጵያ ህንጻ ኮንስተራክሽን፣ ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ኮርፖሬሽን ጋር ውል በመውሰድ የተለያዩ የቅድመ ትግበራ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የሚተገበረው የዩኒቨርሲቲው መሪ ዕቅድ እንከን አልባ እንዲሆን ለማድረግ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራርና አጠቀላይ ማህበረሰብ ቢጨመሩ ወይም ቢስተካከሉ ያሏቸውን ሀሳቦች በወርክሾፖችና በተለያዩ የምክክር መድረኮች አስተያየት እንዲሰጡ ምቹ ሁኔታዎች ተመቻችቷል፡፡ በተጨማሪም በጎንደርና አካባቢው የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ሌሎች አጋር አካላት በሬድዮ፣ በስልክና በኢ-ሜል ስለተቋሙ ይበጃል ያሉትን አስተያየት እንዲሰጡ መደረጉን በተለያየ መልኩ መዘገባችን ይታወቃል፡፡
[widgetkit id=7797]
በመቀጠል ኮርፖሬሽኑ ከተለያዩ አካላት የተገኙትን ግብዓቶች በመሰደር፣ ጥናት በማድረግና ሳይንሳዊ እውቀት በመጨመር እንዲሁም ትንታኔ በመስጠት ከ5 ወር በኋላ የዩኒቨርሲቲውን የምድረ ግቢ ዲዛይን መሪ ዕቅድ የመጀመሪያ ዙር የንድፍ ስራ ህዳር 26/2010 ዓ.ም ይዞ መጥቷል፡፡
በመጀመሪያው ቀን መሪ ዕቅዱን ለማዘጋጀት ውል የወሰደው ድርጅት ከዚህ በፊት የተሰጡትን ሀሳቦችና አስተያየቶች መነሻ በማድረግ ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻና ለሌሎች ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በአጼ ቴዎድሮስ ግቢ ድህረ ምረቃ አዳራሽ ኮርፖሬሽኑ ይዞት የመጣውን ግብረ መልስ በሙያተኞቹ በኩል በገለጻ አስረድቷል፤ ገለጻውን መነሻ በማድረግ ውይይት ተደርጓል፤ ተሳታፊዎችም ያላቸውን ተጨማሪ ሀሳብና አስተያየት ለግሰዋል ፡፡ በሚቀጥለው ቀን/ ህዳር 27/2010 ዓ.ም ኮርፖሬሽኑ ከዩኒቨርሲቲው መካከለኛ አመራሮች ጋር ተመሳሳይ ውይይት ካደረገ በኋላ የዩኒቨርሲቲው ግቢዎች ለተጨማሪ ግብዓት በአካል እንደሚጎበኙ በውይይቱ ተገልጿል፡፡
አቶ አማረ ሰጠኝ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምህንድስና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እንደተናገሩት፣ ዩኒቨርሲቲው ያለውን ሀብት በአግባቡ እንዲጠቀምና የተቋሙን ግቢዎች ስርዓት ባለው መልኩ እርስ በእርስ ለማስተሳሰርና ለማዋቀር እንዲቻል የአዲሱ መሪ እቅድ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አዲሱ የዩኒቨርሲቲው መሪ እቅድ በሀገሪቱ ባሉ የኒቨርሲቲዎችና ከተሞች በበለጠ ሁኔታ ሳይንሳዊ ሂደቱን ተከትሎ የሚሰራ በመሆኑ ለዩኒቨርሲቲውና ለጎንደር ከተማ ጥሩ ገጽታ እንደሚሆን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አቶ አማረ ተናግረዋል፡፡ ዳይሬክተሩ ከአሁኑ/ከመጀመሪያው ዙር የንደፈ ሀሳብ ግምገማ የተለያዩ ግብዓቶችን በመሰብሰብ ከዚያም ከ4 ወር በኋላ እንድ የመጨረሻ የንድፈ ሀሳብ ግምገማ ከተደረገ ከ1 ወር በኋላ የመጨረሻው የዩኒቨርሲቲው የምደረ ዲዛይን መሪ ዕቅድ እርክክብ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
ከዩኒቨርሲቲው ራዕይ ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችልና የማህበረሰቡን ችግር በግንባር ቀደም ሊፈታ የሚያስችል እንዲሁም የአካባቢውን ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ መሪ እቅድ መሆኑን የጠቆሙት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ በመሪ ዕቅዱ የዝግጅት ሂደት መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ደሳለኝ ኮርፖሬሽኑ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ፣ የአካባቢው ነዋሪዎችና አጋር አካላት እንዲሳተፉ እድል የሰጠ ከመሆኑ በጨማሪ ለስራው በቂ ጊዜና ልዩ ትኩረት በመስጠት ያሳየው ቁርጠኝነት የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ለመጪ 20 ዓመታት እንዲያገለግል ተስፋ የተጣለበት ይህ የዩኒቨርሲቲው የምደረ ዲዛይን መሪ ዕቅድ ለሌሎች የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎችና ከተሞች እንደ ተሞክሮ ሁኖ ሊያገለግል እንደሚችል ፕሬዝዳንቱ ያላቸውን ሙሉ እምነት ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አምሳሉ ግዛቸው
የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

