የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የክሊኒካልና አዕምሮ ጤና አጠባበቅ ተማሪዎች ተመረቁ
የጎንደር ዩኒቨርስቲ ከአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር በመተባበር በተቀናጀ የክሊኒካልና አዕምሮ ጤና አጠባበቅ በ2009 ዓ.ም በማስተርስ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 23 ምሩቃን መስከረም 20/2010ዓ.ም አዲስአበባ በግዮን ሆቴል አዳራሽ በደማቅ ሁኔታ አስመረቀ፡፡
ዩኒቨርሲቲው ባለፈው ሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም መግቢያ ላይ በሁሉም ኮሌጆች፣ ኢንሰስቲቲዩት፣ ፋካልቲዎችና ትምህርት ቤቶች፣ በመደበኛ፣ በተከታታይና በክረምት መርሃ ግብሮች፣ባጠቃላይ ከ6500 በላይ ተማሪዎችን በደማቅ ሁኔታ አስመርቋል፡፡
[widgetkit id=7059]
እንዲሁም መስከረም 13/2010 ዓ.ም ደግሞ 207 የህክምና ተማሪዎች እጅግ ደማቅ በሆነ ስነስርዓት ተመርቀዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መስከረም 20/2010ዓ.ም ከአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር በመተባበር በተቀናጀ የክሊኒካልና አዕምሮ ጤና አጠባበቅ የማስተርስ ዲግሪ ፕሮግራም የተከታተሉ 23 ሰልጣኞች ተመርቀዋል፡፡በምረቃ ስነስርዓቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተወካይና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ዳንኤል ገ/ሚካኤል፤ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፐሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ፤የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራአስፈፃሚ አቶ ኢዳኦ ፌጆ ፤ የሆስፒታሉና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላትና የተመራቂ ወላጆች ተገኝተዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፐሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ በምረቃ ስነስርዓቱ ባደረጉት ንግግር ተመረቂዎችንና ወላጆችን ‹‹እንኳን ደስ አላችሁ›› ካሉ በኋላ ስለ አዕምሮ ጤንነት ያሉ እውነታዎችን በተመለከተ ሲናገሩ፤
‹‹ እንደ አለም ጤና ድርጅት አገላለፅ በዓለም ላይ ከ 4 ሰዉ እንድ ሰዉ በአዕምሮ ጤና ችግር ተጠቂ ነዉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአለም ላይ ወደ 450 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በአዕምሮ ችግር እየተጠቁ እንደሚገኙም ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ ከ 1 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በየአመቱ ራሳቸዉን ያጠፋሉ፡፡ ይህ አሃዝ የችግሩን ግዝፈት ያሳያል፡፡ መንግስትም ይህን ችግር ለመቅረፍ የአዕምሮ ጤና ስትራቴጂ ቀርጾ እየሰራ ይገኛል፡፡ ስትራቴጂዉን ለማሳካት ደግሞ በሙያዉ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ በዚህ ረገድ ለዘርፉ የሚሆኑ ባለሙያዎችን በብዛትና በጥራት ለማፋራት በእኛ በኩል ወሳኝ የሚባሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ›› ብለዋል፡፡ አያይዘውም ‹‹ ከዚህ በፊትም ሆነ ወደፊት ዩኒቨርስቲያችን በዘርፉ ጥራት ያለውና ተግባር ተኮር ትምህርት በመስጠት፣ ምርምርና ጥናት በማካሄድና የህብረተሰብ አገልግሎት በመስጠት ፤በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን የአዕምሮ ጤና ችግር ለመፍታት የሚችሉ ዜጐችን በማፍራት የማህበረሰቡን የጤና አገልግሎት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሰራ ፤ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በቀጣዮቹ ዓመታት በአገሪቱ በአዕምሮ ጤና ቀዳሚው የትምህርት፣ የአዕምሮ ጤና አገልግሎትና የህብረተሰቡን ችግር ፈች የሆነ የምርምር ስራ የሚከናወንበት ዘርፍ እንዲሆን ጠንክረን አንሰራለን›› ብለዋል፡፡
የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራአስፈፃሚ አቶ ኢዳኦ ፌጆ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ‹‹ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በመተባበር በተቀናጀ የክሊኒካልና አዕምሮ ጤና አጠባበቅ በማስተርስ ዲግሪ ከ 2002 ዓ.ም ጀምሮ ተማሪዎችን በማሰልጠን ላይ ይገኛል ፡፡ በዚህ የስልጠና ዘርፍ ሁለቱም ወገኖች የጀመሩት የጋራ ትብብር ለስኬት ይበቃ ዘንድ በሁሉም ተቋማት ከከፍተኛ አመራሮች ጀምሮ የተሰጠው ልዩ ትኩረት ውጤታማ እንደነበር በርካታ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ፡ በአጠቃላይ ተመጋጋቢነት ያለው የሁለትዮሽ የሆኑ ተግባራትን በማከናወን ላይ ነን ብሎ መናገር ይቻላል፡፡›› ካሉ በኋላ
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተወካይና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ዳንኤል ገ/ሚካኤል ለእለቱ ተመራቂዎች ንግግርና የስራ መመሪያ የሰጡ ሲሆን ‹‹ ተመራቂዎች ይኸው ዛሬ ለመጀመሪያዉ ምዕራፍ ስኬት ደርሳችኋል፤ ባገኛችሁት ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅማችሁ ለዚህ ላበቃችሁ ህዝብ ትርጉም ያለው አስተዋፅኦ ለማበርከት ፍፁም የተግባር ሰው መሆን ይጠበቅባችኋል፡፡ በተለይ የእናንተ ሙያ ከሰው ህይወት ጋር የሚገናኝ እንደመሆኑ ለሙያችሁና ለገባችሁት ቃል ኪዳን ታማኝ በመሆን፣ ህዝብን ለማገልገልና ከምትሰጡት አገልግሎት እርካታን የምትሹ ፍፁም ታማኝ፣ አዛኝና ሩህሩህ እንድትሆኑ፤ ባጠቃላይ ቃል ኪዳን አክባሪ ለአገር ተቆርቋሪ የልማትና እድገት ቆራጥ አርበኛ እንድትሆኑ በዚህ አጋጣሚ አደራ እላለሁ፡፡››ብለዋል፡፡
በሁለቱም ተቋማት መካከል አሁን ያለው ቅንጅት እና የትብብር እንቅስቃሴ ከዚህ በበለጠ በስፋት በጋራ ለመስራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ የተፈጠረ መሆኑን የሚያመላክት እንደሆነና ይህንን ቀጣይ በማድረግ ረገድ በዩኒቨርሲቲውም ሆነ በሆስፒታሉ በኩል ፅኑ ፍላጎት መኖሩን ያነጋገርናቸው የሆስፒታሉና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ገልፀዋል፡፡
የተመራቂ ተማሪዎችን ቁጥር በተመለከተ በዕለቱ 23 ተማሪዎች የተመረቁ ሲሆን ከዚህ በፊት ከተመረቁ 164 ባለሙያዎች ጋር እስካሁን በጠቅላላ 187 ባለሙያዎች የተመረቁ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል
ዘገባ ደምሴ ደስታ

