የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የ2008 ዓ.ም የተማሪዎች የምረቃ በዓል በደማቅ ስነስርዓት ተከናወነ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የ2008 ዓ.ም የተማሪዎች የምረቃ በዓል ሰኔ 25/ 2008 ዓ.ም ክቡር አምባሳደር ታየ አፅቀስላሴ የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ እና የዕለቱ የክብር እንግዳ ፤ክቡር አቶ ተቀባ ተባባል የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ፤ የዩኒቨርሲቲው የስራ አመራር ቦርድ አባላት፤ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር አመራር አካላት፤ የዩኒቨርሲቲው አጋር ድርጅቶች ፤የእጩ ተመራቂ ወላጆች ፤ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት በተገኙበት ደማቅ በሆነ ስነስርዓት ተከብሯል፡፡
በዘንድሮው የምረቃ በዓል በሁሉም ኮሌጆች፤ ኢንስቲቲዩት፤ ፋካልቲዎችና ትምህርት ቤቶች፤ በመደበኛ፣ በተከታታይና በክረምት መርሃ ግብሮች ፤ በመጀመሪያ ዲግሪ ወንድ 3861 ሴት 1811 በድምሩ 5672፤ በሁለተኛ ዲግሪ ወንድ 370 ሴት 139 በድምሩ 509 ባጠቃላይ 6181 ተማሪዎች የተመረቁ ሲሆን፤ በመምህራን ከፍተኛ ዲፕሎማ ወንድ 144 ሴት 19 በድምሩ 163 መምህራን ተመርቀዋል፡፡
በዚህ የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ባደረጉት ንግግር “የነገ የሀገራችን ተስፋ የሆኑት ዕጩ ተመራቂዎች፤ በዚህ ልዩ የምረቃ እለት እንዲህ ደምቀው፤ አበባ መስለው ስንመለከታቸው ደስታቸው የሁላችንም ደስታ በመሆኑ ለእጩ ምሩቃን፤ ለተመራቂ ቤተሰቦች፤ ባጠቃላይ ለዚህ ደማቅ የዩኒቨርሲቲያችን የምረቃ በዓል ስነ-ስርዓት ታዳሚ ለሆናችሁ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ ፤ እንኳን ደስ አለን፤ እላለሁ” ካሉ በኋላ፡፡
“የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሃገራችን በቀዳሚነት የጤና ሙያተኞችን ለማፍራት የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ኮሌጅና ማሰልጠኛ ማዕከል በሚል ስያሜ በ1947 ዓ.ም እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ከተመሰረተ ከ62 ዓመታት በላይ እየሆነው ነው፡፡ በእነዚህ ዓመታት ጉዞ ዩኒቨርሲቲው የሕዝቡን የጤና ችግር የሚቀርፉ መካከለኛ እና ከፍተኛ የጤና ባለሙያዎችን በማፍራት፤ ወደ ሙሉ ዩኒቨርሲቲነት ከተሸጋገረ ወዲህ ደግሞ ከጤና ሙያተኞች በተጨማሪ በሌሎች ዘርፈ ብዙ ሙያዎች ምሁራንን በማፍራት የሀገራችንን የተማረ የሰዉ ኃይል ፍላጎት በማሟላት ረገድ የበኩሉን ድርሻ በብቃት እየተወጣ ያለ የትምህርት ተቋም ነዉ፡፡ ዛሬ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፍሬዎች ከሃገር እስከ ዓለም አቀፍ ደረጃ የስኬት ቁንጮ ላይ የደረሱ የሕዝብን ችግር በምርምር የፈቱ እዉቅ ሳይንቲስቶች ለመሆን ለመብቃታቸዉ ብዙ እማኝ ጠቅሶ መናገር ይቻላል” ብለዋል፡፡
ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ዩኒቨርሲቲው አሁን ያለበትን ቁመና ጠቅለል አድርገው ሲጠቅሱ “በፕሮግራም ደረጃ፤ ሲጀመር ከነበሩት ሶስት የዲፕሎማ ፕሮግራሞች አሁን ላይ ወደ 67 የሚጠጉ የቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞችና ከ95 በላይ የድህረ-ምረቃ ፕሮግራሞች ደርሰናል፤ ይህም ሶስተኛ ዲግሪን ጨምሮ ማለት ነዉ፡፡ ሃምሳ ያህል በሚሆኑ ተማሪዎች የጀመረው ስልጠና ዛሬ ከሰላሳ ሽህ በላይ ተማሪዎችን በሁሉም መርሃ-ግብሮቻችን ተቀብለን ማስተማር ችለናል፡፡ ጥቂት ተማሪዎችን ከማስመረቅ ተነስተን በየዓመቱ አምስት ሸህ ያህል ተማሪዎችን እንዲህ እንደዛሬዉ የምናስመርቅበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ በአንድ ግቢ የተጀመረው የማሰልጠን ስራ ዛሬ ላይ የዩኒቨርሲቲውን የኮሚኒቲ ትምህርት ቤትና አዘዞ የሚገኘዉን የ620 መምህራን መኖሪያ አፓርታማ ጨምሮ የሰባት ትልልቅ ግቢዎች ባለቤት ሆነናል፡፡ ከ62 ዓመት በፊት ከመቶ ሽህ ብር ዓመታዊ በጀት ተነስተን ዛሬ ከአንድ ቢሊየን በላይ ዓመታዊ በጀት ደርሰናል፤ ሲጀመር የነበሩት መምህራንና በአመራር ቦታ ይሰሩ የነበሩት የውጪ ዜጎች ነበሩ፡፡ አሁን ሁሉም አመራሮችና ከ95 ከመቶ በላይ መምህራን ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ በጣት በሚቆጠሩ መምህራን የጀመረዉ ተግባር ዛሬ፤ ከአንድ ሽህ ሰባት መቶ በላይ ለዛውም አብዛኛዎቹ የሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ ባለቤቶች የሆኑበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከመምህራን ቁጥር ጋር ተጨምሮ ስድስት ሽህ ያህል ሰራተኞችን ይዞ አገርና ህዝብን የሚጠቅሙ አያሌ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል” ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ዶ/ር ደሳለኛ መንገሻ በማጠቃለያ ንግግራቸውም፤ ለተመራቂ ተማሪዎች፤ “እናንተ ዛሬ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ለመጀመሪያዉ ምዕራፍ ስኬት በመብቃታችሁ ዉስጣችሁ ያለዉ ደስታና ሃሴት እንዳለ ሆኖ፤ ባገኛችሁት ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅማችሁ ለዚህ ላበቃችሁ ህዝብ ትርጉም ያለው አስተዋፅኦ ለማበርከት ፍፁም የተግባር ሰው መሆን ይጠበቅባችኋል፡፡ አገራችን የተያያዘችውን የልማትና የዕድገት ጎዳና ለማስቀጠል፤ የተጀመረው የህዳሴ ጉዞ እውን እንዲሆንና ጅምሩ ፀረ-ድህነት ትግላችን ዳር እንዲደርስ ሚናችሁ በእጅጉ ጉልህ መሆኑን ልብ ልትሉ ይገባል፡፡ የመማር ውጤት የሚለካው በአገር ዕድገትና በህዝብ ኑሮ ላይ በሚመዘገብ ለውጥ ነው፡፡ ይህ እውን የሚሆነው ደግሞ እናንተ ሙስናን፤ ብልሹ አሰራርንና ኢ-ስነምግባራዊ ድርጊቶችን ለመዋጋት በቁርጠኝነት በመሰለፍ በዛሬዋ እለት የምትገቡትን ቃል ስትጠብቁ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ቃል ኪዳን አክባሪ፣ ለአገር ተቆርቋሪ የልማትና እድገት ቆራጥ አርበኛ እንድትሆኑ አደራየ ጥብቅ ነው” ብለዋል፡፡
በስነስርዓቱ ዶ/ር ብርቁ ደሞዝ የዩኒቨርሲቲው ዋና ሪጂስትራር አማካኝነት የሁሉም ኮሌጅ፤ ኢንስቲቲዩት፤ ፋካሊቲና ትምህርት ቤት ዲኖች አቅራቢነት በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ዕጩ ተመራቂዎች እየቀረቡ የተመረቁ ሲሆን የዕለቱ የክብር እንግዳ ክቡር አምባሳደር ታየ አፅቀስላሴ የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ባደረጉት ንግግር፤ በክብር እንግድነት የጋበዛቸውን ጎንደር ዩኒቨርሲቲን አመስግነው፤ በምረቃ በዓል ላይ በተመራቂነትም ሆነ ባስመራቂነት መገኘት የሚሰጠውን ውስጣዊ የሆነ የመንፈስ እርካታ አንስተው ደስታው የሁላችንም ስለሆነ እነኳን ደስ አለን ካሉ በኋላ፤ለተመራቂ ተማሪዎች የህይወት ስንቅ የሚሆን የራሳቸውን ተሞክሮ በስፋት አቅርበው፤ እውቀት፤ ክህሎት፤ ልምድና ተሞክሮ በሂደት የምናዳብረው ሆኖ አገርንና ህዝብን መውደድ ፤ለሀቅ መቆም፤ ድህነትን ለመዋጋት ቆራጥ መሆን፤ ከምንም በላይ ሙስናን መጠየፍ እንደሚገባቸው ለተመራቂዎቹ አደራ ብለዋል፡፡ የክብር እንግዳው በዓመቱ ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎችም የመዳሊያና የዋንጫ ሽልማትም ሰጥተዋል፡፡
በምረቃ ስነስርዓቱ መርሀ ግብር መሰረትም የምስጋናና የእውቅና ሽልማት ፤በክቡር አቶ ተቀባ ተባባል የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተሰጥቷል፡፡ በአዲሱና ከ1000 በላይ የህሙማን መኝታ አልጋ ያለዉ በመንግስትና በአጋር አካላት የተገነባዉ የዩኒቨርሲቲዉ ሪፈራል ሆስፒታል ህንፃ ስራዉ በተሟላ መንገድ እንዲጀምር ለማድረግ በመንግስትና በአጋር ድርጀቶች ድጋፍ ሰፊ ስራ እየሰራን ያለ ሲሆን፤ በአሜሪካ መንግስት ድጋፍ የተገነባው የተመላላሽ ህክምና መስጫ ዘመናዊ ህንፃ በዚህ ዓመት ስራ ጀምሯል፡፡ ለዚህ ሆስፒታል አገልግሎት ስዊድን አገር ከሚገኝ ሂዩማን ብሪጅ ከተሰኘ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ግምቱ ሰላሳ ሚሊየን ብር የሆነ የ1000 ዘመናዊ የህሙማን አልጋና የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ ተገኝቷል፡፡ ለዚህ ትልቅ ተግባር ለግብረ ሰናይ ድርጅቱ፤ በግንኙነቱ ሂደት ግንባር ቀደም ለሆኑት አቶ አዳሙ አንለይ የሂዩማን ብሪጅ ካንትሪ ዳይሬክተርና፣ ዶ/ር ሮበርት በርማንን ላደረጉት ታላቅ ድጋፍ የምስጋናና የእውቅና ሽልማት ተሰጥቷል፡፡ ይህንን ስነስርዓት ያስፈፀሙት ዶ/ር ታከለ ታደሰ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፤ በዓመቱ ምርጥ ተማሪነትም ተማሪ ጎሹ ኔንቆ በህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፤ ከሳይካትሪ ትምህርት ክፍል ተሸላሚ ሆኗል፤ ይህንንም ስነስርዓት አቶ ሰለሞን አብርሃ የአስተዳደር ምክትል ፐሬዚዳንቱ አስፈፅመውታል፡፡
በምረቃ ስነስርዓቱ፤ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በ62 ዓመታት ጉዞው ከ50 ሽህ በላይ ምሩቃንን ለአገርና ለዓለም ያበረከተ አንጋፋ ተቋም በመሆኑ በዚህ እውቅ ዩኒቨርሲቲ ልጆቻቸው ተምረው በመመረቃቸው ደስተኛ መሆናቸውን አብዛኛዎቹ የተመራቂ ወላጆች አስተያየታቸውን ሰጥተውናል፡፡
የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ( ጎንደር ዩኒቨርሲቲ)
ሰኔ 26/2008 ዓ.ም