የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የ60 ዓመት ጉዞ አጭር ቅኝት
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሃገራችን በቀዳሚነት የጤና ሙያተኞችን ለማፍራት የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ኮሌጅና ማሰልጠኛ ማዕከል በሚል ስያሜ በ1947 ዓ.ም እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ከተመሰረተ ድፍን 60 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡
በሀገራችን የጤና ሙያተኞችን ለማሰልጠን በቀዳሚነት የተቋቋመው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከአመሰራረቱ ጀምሮ በሂደት በተለያዩ ስያሜዎች በእድገት ጎዳና እየተጓዘ ዛሬ በሀገራችን ከሚገኙት ታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎች ተርታ መሰለፍ የቻለ፤ በርካታ ታዋቂ ምሁራንን ለሀገር በማበርከት አኩሪ ታሪከዊ ረጅም ጉዞ የተጓዘና በመማር ማስተማሩ፤ በምርምሩና በማህበረስብ አገልግሎቱ ውጤታማ ተግባር ያከናወነ አንጋፋ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለሀገር ዕድገትና ለህዝቦች ኑሮ መሻሻል ፋይዳ ባላቸው የትምህርት መስኮች በአንደኛ፣ በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ትምህርት ይሰጣል፤ የህብረተሰብ ችግር ፈቺ ምርምር ያካሂዳል፡፡ የህብረተሰብ አገልግሎት በስፋትና በጥራት ይሰጣል፡፡ ይህ አይነት ነባራዊ ሁኔታን ግምት ውስጥ ያስገባና የህዝብን ሕይወት ለመለወጥ የቆመ ተቋም ደግሞ ያለጥርጥር የአንድ ሃገር እምቅ ሀብት ነው፡፡
የዚህን አንጋፋ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፋይል ለማስቃኘት ወደኋላ ተመልሰን ከአመሰራረቱ ታሪክ ስንጀምር፤ በ1945 ዓ.ም በደምቢያ ወረዳ የወባ ወረርሽኝ ተከስቶ ቁጥሩ ብዙ የሆነ ህዝብ ለህልፈት መዳረጉ በዛ ጊዜ የታየ መራራ ትዝታ እንደሆነ አሁን ድረስ የእድሜ ባለፀጎች የሚያወሱትን ክስተት እናገኛለን፡፡ ከቆላድባ ከተማ አስራ ስምንት ኪሎ ሜትር ጀምሮ እስከ ጣና ሃይቅ ሰሜናዊ ጠረፍ የተንጣለለው ሜዳ በክረምት ወቅት ዝናብን ተከትሎ ጎርፍ የሚተኛበት ስፍራ እንደመሆኑ ለወባ ወረርሸኝ የተጋለጠ ነው፡፡ በመሆኑም በተጠቀሰው ዘመን ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ከሰባት ሽህ በላይ የሚሆኑት በተከሰተው የወባ ወረርሽኝ እንዳለቁ በታሪክ ተፅፎ እናገኛለን፡፡
ከ1942-1943 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ደግሞ በዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ኢትዮጵያ የተማሩ የጤና ሰራተኞች እንደሚያስፈልጓትና መፍትሄውም የረጅም ጊዜ የጤና አጠባበቅ ትምህርት ሊሰጥ የሚችል የማሰልጠኛ ተቋም ሊከፈት እንደሚገባም የሚጠቁም ሃሳብ የቀረበበት ወቅት ነበር፡፡ ለአፈፃፀሙም ኢትዮጵያዊ ወጣቶችን በመመልመልና ወደ ወዳጅ የባህር ማዶ ሀገራት ትምህርት እንዲቀስሙና ጎን ለጎንም የጤና አጠባበቅ ሰራተኞችን በዝቅተኛና መካከለኛ ደረጃ የሚያሰለጥን ተቋም አገር ውስጥ እንዲቋቋም ተወሰነ፡፡
በ1945 ዓ.ም በደምቢያ ወረዳ የተከሰተው የወባ ወረርሽኝና እልቂት ደግሞ የዕቅዱን ማረፍያ በጣሊያን የተሠራውንና በቀላሉ በሠራተኛ ሊሟላ የሚችለውን የጎንደር ሆስፒታል እንዲሆን አደረገ፡፡
የማህበረሰብ ጤና ኮሌጅና የስልጠኛ ማዕከልን ለማቋቋም የተደረገው ስምምነት በኢትዮጵያ በኩል በወቅቱ የጤና ተጠባባቂ ሚኒስቴር በነበሩት መርስዔ ሃዘን ወ/ጊዮርጊስና የአሜሪካን መንግስት ወክለው በመጡት የኢትዮጵያ የቴክኒክ ድጋፍ ዳይሬክተር ጀምስ ጎርደን በሚያዝያ 21/1946 ዓ.ም ስለመፈረሙም መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ በዚህም ሂደት የጎንደር የህዝብ ጤና አጠባበቅ ኮሌጅና ማሰልጠኛ ማዕከልም በ1947 ዓ.ም በይፋ ተመሰረተ፡፡ የዚህ ተቋም መቋቋምም በመላው ኢትዮጵያ ባለው የጤናው ዘርፍ ላይ ጉልህ አሻራ ያሳረፈና አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ሆነ፡፡
እንግዲህ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሃገራችን በቀዳሚነት የጤና ሙያተኞችን ለማፍራት የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ኮሌጅና ማሰልጠኛ ማዕከል በሚል ስያሜ በ1947 ዓ.ም እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ከተመሰረተ እነሆ ድፍን 60 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡
በዚህ የ60 ዓመታት ጉዞ፡-
– በጅማሮዉ ምዕራፍ የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ኮሌጅና የማሰልጠኛ ማዕከል
– በሁለተኛዉ ምዕራፍ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ
– በሶስተኛዉ ምዕራፍ አሁን እስካለበት ጊዜ ድረስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሚሉ የተለያዩ ስያሜዎች የተለያዩ ምዕራፎችን አልፏል፡፡
በ1947 የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ኮሌጅና የማሰልጠኛ ማዕከል ሲቋቋም 50 ያህል የጤና ባለሙያዎችን በጤና መኮነንነት፤ በኮሚኒቲ ነርስነትና በአካባቢ ጤና ተቆጣጣሪነት በማሰልጠን ነበር የጀመረው፡፡ በፕሮግራም ደረጃ፤ ሲጀመር ከነበሩት ሶስት የዲፕሎማ ፕሮግራሞች አሁን ላይ ወደ 64 የቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞችና ሶስተኛ ዲግሪን ጨምሮ ከ76 በላይ የድህረ-ምረቃ ፕሮግራሞች ደርሷል፡፡ ዛሬ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አራት ኮሌጆች፣ ሶስት ፋካሊቲዎችና ሁለት ትምህርት ቤቶች ያሉት ሲሆን፤ ሃምሳ ያህል በሚሆኑ ተማሪዎች የጀመረው ስልጠና ዛሬ ወደ ሃያ ስድስት ሽህ ተማሪዎችን በሁሉም መርሃ-ግብሮቻችን ተቀበሎ ማስተማር ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ጥቂት ተማሪዎችን ከማስመረቅ ተነስቶ በየዓመቱ አምስት ሸህ ያህል ተማሪዎችን የሚያስመርቅበት ወቅት ላይ ይገኛል በእስካሁኑ ሂደትም አርባ ሸህ የሚደርሱ ምሁራንን ለማፍራት የቻለ ትልቅ ተቋም ነው፡፡
አሁን 60 ዓመት የሞላዉ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ከመማር ማስተማሩ ጎን የምርምርና የተለያዩ የማህበረሰብ አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ዩኒቨርቲያችን ከአንድ ኮሊጅነት ወደ አራት ኮሌጆች፣ ሶስት ትምህርት ቤቶችና ሁለት ፋካልቲዎች አድጓል ያ ማለት ከአሁን ቀደም በህክምናና ጤና ሳይንስ ዙሪያ ብቻ ይሰሩ የነበሩ ምርምሮችና ሲሰጥ የነበረዉ የማህበረሰብ አገልግሎት በተለያዩ ኮሌጆች፣ ፋካልቲዎችና ትምህርት ቤች ባሉ ምሁራንም እንዲሰጥ ጥሩ አጋጣሚን ፈጥሯል፤ በዚህ አግባብ ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ ምርምሮችና የማበረሰብ አገልግሎቶች በርከት እያሉ የመጡበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡
በዚህ አግባብ ለ60 ዓመታት የተሰሩ ምርምሮችንም ስንቃኝ በመጀመሪያዎቹ አርባ እና ሃምሳ ዓመት ይሰሩ የነበሩ ምርምሮች በመምህራኑ በጎ ፈቃድና ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ ነበሩ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ምርምሮች የሚሰሩት በትኩረት አቅጣጫዎች ተለይተዉ በተቀመጡ በተለዩ የምርምር አጀንዳዎች ሊሆን ስለሚገባዉ፤ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምር የትኩረት አቅጣጫዎችን የዛሬ አራት ዓመት ገደማ ለይቶ ምሁራኑ በተለዩ የትኩረት አቅጣጫዎች መሰረት የምርምር ስራዎቻቸዉን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው የምርምር ፖሊሲ አለዉ፡፡ በዩኒቨርሲቲው የምርምር ፖሊሲ መሰረት ምርምር በቡድን የሚሰራበትን አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ሌላው የዩኒቨርሲቲው የምርምር ፖሊሲ በሚፈቅደው መሰረት ምርምር ሊሰራ የሚገባዉ በዘፈቀደ ሳይሆን በተለዩና ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ እንዲሆን የምርምር አጀንዳዎች (Thematic Areas) ተለይተዋል፡፡ ሌላው የዩኒቨረሲቲው የምርምር ፖሊሲ ደግሞ ምርምሮች የሚሰሩት ችግር መፍታት ስለሚገባቸዉ ነዉና የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ሊሆን ይገባል የሚል ነው፡፡ በእነዚህ ሶስት ትልልቅ መርሆዎች መሰረት አሁን ዩኒቨርሲቲው ዉስጥ ምርምር እየተሰራ የሚገኘዉ፡፡ ይህ አዲስ የዩኒቨርሲቲው የምርምር አካሄድ የመምህራንን የምርምር ተነሳሽነት ከፍ እንዲል በማድረጉ፤ ባለፉት አራት አመታት ዉስጥ ብቻ በመምህራን ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ የምርምር ንድፈ-ሃሳቦች ለዩኒቨርሲቲዉ ቀርበዋል፡፡
መንግስት የሚመድበዉ የምርምር ድጋፍ በጀትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ የዛሬ አስር ዓመት ዩኒቨርሲቲያችን ዩኒቨርሲቲ ሆኖ ሲፈጠር የነበረን ዓመታዊ የምርምር በጀት ድጋፍ 200 ሺህ ብር ያህል ነበር፡፡ ከዛሬ አራት አመት ጀምሮ የፕሮግራም በጀትን ተጠቅመን ወደ ስራ ከገባን በኋላ የምርምር በጀታችን አንድ ሚሊየን፤ ቀጥሎ ስድስት ሚሊየን ከዛ ወደ ሰባት ሚሊየን፤ ዘንድሮ ደግሞ ወደ 9.5 ሚሊየን ገደማ ደርሶ በርካታ የምርምር ስራዎች እንዲሰሩ አስችሏል፡፡
የምርምር ስራዎች የህብረተሰቡን ችግር መፍታት ይገባቸዋል ሲባል፤ የተፈቱ የማሀበረሰብ ችግሮች ዉጤቶቻቸዉ ወደ ማህበረሰቡ ቀርቦ፤ ማህበረሰቡና ሌላዉም ባለ ድርሻ አካል መጠቀም ይገባዋል ማለት ነው፡፡ በዚህ ላይ ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የዉይይት መድረኮችን እያዘጋጀ በምሁራን የሚሰሩ የምርምር ስራዎች ለማህበረሰቡና ለሚመለከታቸዉ አጋር አካላት እያቀረበ፤ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራ ነዉ፡፡
በዚህ ሂደት ባለፉት አራት ዓመታት ጊዜ ዉስጥ ወደ 24 የሚሆኑ ሃገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ የምርምር ኮንፈረንሶችና ወርክሾፖች በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ተዘጋጅተዉ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች እና ከተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች የተወጣጡ ምሁራን ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ መጥተዉ እነዚህ የምርምር ጉባኤዎች ላይ በመገኘት ተገቢውን ምሁራዊ እስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡
እነዚህን የምርምር ጉባኤዎችን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዳራሽ ዉስጥ ማካሄድ፤ የዩኒቨርሲቲያችን መምህራን የሰሩትን የምርምር ዉጤት አቻ ከሆኑ መምህራን ጋር ተወያይተዉ የሚማከሩበትና ለቀጣይ ሊሰሩ የሚገቡ ነገሮችን የሚለዩበት ስለሆነ፤ ተጠቃሚዎች፣ ፖሊሲ አዉጭዎች እና ኢምፕልመንተርስ ወይም ተግባር ላይ የሚያውሉት በጉባዔው ስለሚታደሙ፤ የምርምር ዉጤቶችን በዚህ አጋጣሚ ወስደዉ ወደ ተግባር እንዲገቡ ሁኔታዎች ስለሚመቻቹላቸው፤ ከዚህም በተጨማሪ ምሁራኖቻችን ከሌሎች ከአገር ውስጥና ከዓለም ዙሪያ ከመጡ አቻዎቻቸዉ ጋር አብረው የሚሰሩበትን አግባብ ስለሚፈጥሩ፤ ያካሄድናቸው የምርምር ጉባዔዎች ዘርፈ ብዙ ጥቅም ነበራቸው ማለት ይቻላል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ በርካታ የምርምር ጉባዔዎችን ማስተናገዳችን፤ የዩኒቨርሲቲያችን መምህራን የሰሩትን የምርመራ ስራና ዉጤቶቻቸዉን ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባሻገር በዓለም አቀፍና አገር አቀፍ የምርምር ጉባኤዎች ላይ ለማቅረብ እድሉን እንዲያገኙ ከማድረጉም በተጨማሪ በዚህ አግባብ መሄዳችን የምርምር ስራዎቻችን ሊጠቀም እና ሊገለገል ለሚገባዉ አካል እንዲደርስ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡
ተቋም ከተቋም የሚኖርን ግንኙነት በተመለከተ ቀደምት ከሆኑና ልምድ ካላቸዉ ተቋማት ጋር በቅርበት አብሮ በቅንጅት መስራት አስፈላጊ ስለሆነ የጎንደር ዩኒቨርሲቲም በምርመር ዙሪያ ከተለያዩ ተቋማት ጋር አብሮ ለመስራት የተለያዩ የጋራ የመግባቢያ ሰነድ እና ስምምነት ተፈራርመን በስፋት ወደ ተግባር የገባንበት ወቅት ላይ እንገኛለን ፡፡
ዩኒቨርሲቲዉ ህብረተሰቡን ማገልገል ቀዳሚ ዓላማ አድርጎ እንደመመስረቱ፤ ከመማር ማስተማሩና ከምርምር ስራዎች ጎን ለጎን ህዝቡ ዉስጥ ዘልቆ በመግባት ካሉ የህብረተሰቡ ችግሮች ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጠዉን በመለየት በመምህራንና በተማሪዎች የሚሰጠዉ የማህበረሰብ አገልግሎት በብዛት፣ በጥራትና በተደራሽነት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በአመት ከአምስት ሚሊየን ህዝብ በላይ አገልግሎት ያገኝበታል ተብሎ በሚገመተው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል በተመላላሽና ተኝተው ከሚታከሙ ህሙማን በተጨማሪ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ደረጃቸውን የጠበቁ የዓይን ህክምናና ማሰልጠኛ ማዕከል፤ የፌስቱላ ህክምናና ዓለም አቀፍ ማሰልጠኛ ማዕከል፤ መድሀኒት የተለማመደ ቲቪ ህክምና መስጫ፤ ደረጃውን የጠበቀ ልዩ ዋርድ፤ የካላዛር ህክምናና የምርምር ማዕከል እና ሌሎችንም በመክፍትና በማጠናከር የህብረተሰቡን የጤና ችግር በህክምናና በምርምር በመፍታት ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም በአሁኑ ሰዓት በመንግስትና በአጋር አካላት በመሰራት ላይ የሚገኙት የሪፈራል ሆስፒታል ኮምፕሌክስ ህንፃዎች አገልግሎት ሲጀምሩ የህብረተሰብ አገልግሎቱ የላቀ እንደሚሆን የሚያጠራጥር አይደለም፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች በአርአያነት ሊነሳ የሚገባው ደግሞ የህግ ድጋፍ በገንዘባቸው ማግኘት ለማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ማለትም ለአረጋውያን፤ ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ ህፃናትና ሴቶች እንዲሁም ከኤች አይቪ ጋር ለሚኖሩ ወገኖች በዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ቤት መምህራንና ተማሪዎች ነፃ የህግ ድጋፍ የሚሰጡ በተለያዩ ወረዳዎች 13 ማዕከላት ተቋቁመው አገልግሎት እየተሰጠ ሲሆን ወደፊትም ተግባሩ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ሌላው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሲ.ቢ.አር ፕሮግራም ሲሆን፤ ይህ ፕሮግራም በጎንደር ከተማ የሚገኙ አካል ጉዳተኞችን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ እና የተለያዩ የመንግስት ተቋማት አገልግሎታቸዉ ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ማድረግ እንዲችሉ ድጋፍ የሚያደርግ ተቋም ነዉ፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሲ.ቢ.አር ፕሮግራም በሰሜን ጎንደር ዞን በሚገኙ 11 ወረዳዎች አካል ጉዳተኛ የማህበረሰቡ ክፍሎችን በተለያዩ ልማታዊ ዘርፎች ይኸውም በትምህርት፣ በጤና፣ በገቢ ማመንጫ፣ በማህበራዊ እና ራስን የማስቻል ዘርፎች በሰፊው ሲደግፍ፣ ሲያበረታታና ልዩልዩ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በአሁኑ ስዓት በዩኒቨርሲቲዉ እየተሰጡ ያሉ የማህበረሰብ አገልግሎቶችን ዘርዘር ባለ መንገድ ለማሳየት፤
1. ከላይ ለማንሳት እንደተሞከረው በዩኒቨርሲቲዉ ሪፈራል ሆስፒታል ዘርፈ ብዙ የጤና አገልግሎቶች ይሰጣሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ደረጃቸዉን የጠበቁ፤ የዓይን፤ የፌስቱላ፤ የቲቢ፤ እና መሰል ህክምናዎች ይገኙበታል፡፡
2. በመስክ የቡድን ስልጠና ፕሮግራም በጤናዉ ዘርፍ ተመራቂ ተማሪዎች ከ50,000 (ሃምሳ ሺ) ህዝብ በላይ (Out Reach Health Service) በደባርቅ፤ ዳባት፤ ቆላድባ ፣ አዲስ ዘመን፣ ወረታ፣ ትክልድንጋይ፤ ጭልጋ ወረዳዎች ይሰጣል፡፡
3. በዩኒቨርሲቲዉ ዉስጥ የካላዛር የህክምናና የምርምር ፕሮጀክት አማካኝነት ተረስቶ ለቆየዉ ለዚህ ህመም ህክምና ይሰጣል፤ ምርምርም ይካሄዳል፡፡
4. በዳባት የምርምር ማዕከል በተለዩ ዋና 10 የጤና ችግሮች ትልልቅ ምርምሮች ይካሄዳሉ፤ ተገቢ መረጃዎች ለተመራማሪዎችና ለፖሊሲ አዉጭዎች ይደራጃል፡፡
5. የተከታታይና የርቀት ትምህርት ፕሮግራም ለማህበረሰቡ ይሰጣል፡፡
6. በገንዘብ ጠበቃ ገዝተዉ መከራከር ለማይችሉ የህ/ሰብ ክፍሎች በ13 ማዕከላት ነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ይሰጣል፡፡
ለትምህርት ጥራት ቅድሚያ ሰጥቶ የሚንቀሳቀሰው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከኬጂ አስከ 12ኛ ክፍል የሚያስተምረውን የዩኒቨርሲቲው ኮሚኒቲ ት/ቤት ጨምሮ ከኬጂ እስከ ፒኤችዲ ትምህርት የሚሰጥበት ተቋም ነው፡፡
ለትምህርት ጥራት እንደመታተሩ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተከታታይ ሁለት የትምህርት ጥራት አውደ ጥናቶችን በማስተናገድ ምሁራን በትምህርት ጥራት ዙሪያ እንዲመክሩ ማደረጉ ለትምህርት ጥራት ላለው ቁርጠኝነት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የዩኒቨርሲቲው መምህራን የተለያዩ የቋንቋና የሳይንስ ትምህርት የ2ኛ ደረጃ መምህራንን ተከታታይ ስልጠናዎችን በመስጠት ትምህርት ጥራት ከታች ከመሰረቱ እንዲመጣ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ላይ ይገኛሉ፡፡ የዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራትና ኦዲት ቢሮም ከሚያካሂዳቸው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ የትሬሰር ጥናት በማካሄድ የዩኒቨርሲቲው ምሩቃን ምን ያህል ባገኙት እውቀትና ክህሎት ተጠቅመው አገልግሎት እየሰጡ ለመሆኑ ያደረገው ጥረት ዩኒቨርሲቲው ለትምህርት ጥራት ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ለመሆኑ ሌላው ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
በሴት ተማሪዎች ዙሪያ አቅምን ማጎልበት የተመለከተ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲዉ ሲገቡ በተለይም ሴቶች ከሚያጋጥሟችዉ ችግሮች አንፃር ችግሮችን መቋቋም እንዲችሉ አቀባበል ይደረጋል፣ የሴት ተማሪዎችን Attrition Rate ለመቀነስም በርካታ ስራዎች ይሰራሉ፡፡ በስርዓተ-ፆታ HIV/AIDS እና ልዩ ፍላጎት ጉዳዮች ጽ/ቤት አማካኝነት ለችግረኛ ሴት ተማሪዎች የተለያዩ የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ይደረጋል፣ በሴት መምህራን ማህበር አማካኝነት የሴት ተማሪዎችን አቅም በማጠናከር እና ትምህርታቸዉን በሰላም ተከታትለዉ በተሳካ ሁኔታ እንዲያጠናቀቁ በርካታ ድጋፎች ይደረግላቸዋል፡፡ አነዚህ በርካታ አገርና ህዝብን የሚጠቅሙ እንቅስቃሴዎች በሚደረግበት በአንጋፋው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባሳለፍነው የ2006 ዓ.ም ደግሞ የ60ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡ በክብረ በዓሉ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፤ በርካታ በመላዉ ዓለም የሚገኙ የቀድሞ የዩኒቨርሲቲዉ ተመራቂዎች፤ በአካባቢ፣ በሀገር ዉስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ የተቋሙ ወዳጆች (Friends)፤ አጋርና ተባባሪ አካላት፣ የ2006 ዓ.ም ዕጩ ተመራቂዎችና ወላጆቻቸው፤ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፤ የጎንደርና አካባቢው ነዋሪዎች፤ የዩኒቨርሲቲያችን ማህበረሰብ አባላት የበዓሉ ታዳሚ ሆነዋል፡፡
የበዓሉ መሪ ቃል “ዕድገት፣ ፈጠራ፣ ልማት” የሚሉ ጽንሰ-ሃሳቦች የተካተቱበት ነበር፡፡ ይህንንም መሪ ቃል ስንመርጥ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህብረተሰቡን ቁልፍ፤ ወቅታዊና መሰረታዊ ችግር መፍታትና መልስ መስጠትን መነሻና ቀዳሚ ዓላማ አድርጎ እንደመመስረቱ፤ ዩኒቨርሲቲው ባለፈባቸዉ የተለያዩ ስያሜዎችና ደረጃዎች ዕድገትን ለማምጣት በተለያዩ የለዉጥ ሂደቶች ሲያልፍ ለዕድገት፣ ለፈጠራ፣ ለልማት እየታተረ ለመሆኑ አሁን የሚገኝበት ደረጃ ህያው ምስክር ሊሆን እንደሚችል በመተማመን ነበር፡፡
በዓሉን የማክበር አጋጣሚውን በመጠቀም በ60 ዓመታት ጉዞዉ ዩኒቨርሲቲው ያስመዘገባቸዉን ድሎች ዕዉቅና እንዲያገኙ የማድረግ፣ ለዚህ ዉጤታማ ጉዞ፤ ለድሎችና ለስኬቶች በቀጥታና በተዘዋዋሪ ድጋፍ ላደረጉ አጋር አካላት ዕዉቅና የመስጠት፣ ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ስዓት የሚገኝበትን ደረጃና እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን የማስተዋወቅና በዚህ ወርቃማ አጋጣሚ በመጠቀም የወደፊቱ ስራ ዉጤታማ ይሆን ዘንድ የነበሩ የሃገር ዉስጥና የዉጭ ግንኙነቶችን የማጠናከር፤ አዳዲስ ግንኙነቶችን የመፍጠር፤ ባጠቃላይ የተቋሙን የወደፊት ዕድገት በፅኑ መሰረት ላይ ማቆምን ዋናና መሰረታዊ ዓላማ በማድረግ ተግባራዊ ስራዎች ተሰርተው ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ ስኬታማ ሆነናል፡፡
ባጠቃላይ ዩኒቨርሲቲው አሁን ያለበትን ደረጃ ስንመለከት፤ በአንድ ግቢ የተጀመረው የማሰልጠን ስራ ዛሬ ላይ የዩኒቨርሲቲውን የኮሚኒቲ ትምህርት ቤትና የ620 መምህራን መኖሪያን ጨምሮ የሰባት ትልልቅ ግቢዎች ባለቤት ሆኗል፡፡ ከ60 ዓመት በፊት ሲጀመር የነበሩት መምህራንና መሪዎች የውጪ ዜጎች ነበሩ፡፡ ዛሬ ሁሉም አመራሮችና ከ95 ከመቶ በላይ መምህራን ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ቁጥራቸውም በጣት ከሚቆጠሩ መምህራን፤ በአሁኑ ሰዓት ከአንድ ሽህ አራት መቶ በላይ መምህራን፤ ለዛውም አብዛኛዎቹ የሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ ባለቤቶች የሆኑበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከመምህራን ቁጥር ጋር ተጨምሮ ከአምስት ሽህ በላይ ሰራተኞችን ይዞ አገርና ህዝብን የሚጠቅሙ አያሌ ተግባራትን እየተወጣ ይገኛል፡፡ የምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎት፣ የትምህርት ግብዓቶችን ማሟላትና ኢንፍራስትራክቸርን በማሟላት ረገድም በጣም ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ተዘጋጀ
ነሐሴ 2006 ዓ.ም

