የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ደንቢያ ወረዳ ለሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ት/ምህርት ቤቶች የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በደንቢያ ወረዳ ለሚገኙ የተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ት/ምህርት ቤቶች የሚያገለግሉ በርካታ የቁሳቁስ ድጋፍ በደንቢያ ወረዳ አስተዳደር ፅ/ቤት ኃላፊ በአቶ እያዩ ውድነህ በኩል መስከረም 23/2009 ዓ.ም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ግቢ አስረክቧል፡፡
የቁሳቁስ ድጋፉ የተደረገው የደንቢያ ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት በጠየቀው ትብብር መሰረት ሲሆን፤ በጥያቄው መሰረት ዩኒቨርሲቲው የኮምፒውተር ፣የወንበርና ጠረጴዛ፣ የጥቁር ሰሌዳ፣የኮፒ ማሽን፣ የፕሮጀክተር የቴሌቪዥን፣የፍሪጅና የመሳሰሉት የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡ እነዚህ መገልገያ መሳሪያወችም ለአይንባ፣ለቆላድባ፣ ለጯሂት እና ለጎርጎራ መሰናዶ እና አጠ/2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች እንዲሁም በወረዳው ለሚገኙ የተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች መድረሱንና ወረዳው የነበረበትን ሰፊ የግብዓት ችግር በመቅረፍ ላይ መሆኑን እኛም በቦታው በመገኘት ማረጋገጥ ችለናል፡፡
በተለይ በአይንባ መሰናዶ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የተደረገው የጥቁር ሰሌዳ፣ የተማሪዎች መቀመጫ ወንበር፣ ለመመህራን ማረፊያ እና ለላብራቶሪ ክፍል የሚያገለግሉ በርካታ ወንበሮችን ዩኒቨርሲቲው መለገሱ ት/ቤቱ የነበረበትን ሰፊ የግብአት ችግር በከፍተኛ ሁኔታ የቀረፈላቸው መሆኑን የት/ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ዮናስ ዘለቀ ገልፀዋል፡፡ ርእሰ መምህሩ አክለውም ዩኒቨርሲቲው ወደፊት ትምህርት ቤታቸው ያለበትን የቁሳቁስና የግብአት ችግር ከመቅረፍ ጎን ለጎን የመምህራንንየክህሎት ክፍተት በመሙላት ጭምር ዩኒቨርሲቲው ከጎናቸው እንደማይለይ ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል፡፡
የደንቢያ ወረዳ አስተዳደር ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ እያዩ ውድነህ በበኩላቸው እንደገለፁት በወረዳው የሚገኙ የተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በደረሰባቸው ቃጠሎ ምክንያት ምንም አይነት መገልገያ መሳሪያ እንዳልነበራቸው ገልፀው የጎንደር ዩኒቨርሲቲው ባደረገው ሰፊ የቁሳቁስ ድጋፍ እንደ ፍርድ ቤት ያሉ መስሪያ ቤቶች ስራ መጀመር መቻላቸውን አስረድተው ለዩኒቨርሲቲው በተለይ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ከፍ ያለመስጋና አቅርበዋል ፡፡ አቶ እያዩ አክለውም ዩኒቨርሲቲው ይህን ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር ቁሳቁሱ ቦታው ድረስ እንዲጓጓዝ የትራንሰፖርት አገልግሎት መስጠቱን በመግለፅ ዩኒቨርሲቲው ያለውን ህዝባዊ ወገንተኝነት አድንቀዋል፡፡
ኃላፊው በመጨረሻም ዩኒቨርስቲው ከወረዳው ጋር ቆየት ያለ ትስስር እንደነበረው በማስታወስ ካሁን በፊትም ሊገነባ ታስቦ በነበረው ባለአንድ ፎቅ የአስተዳዳር ጽ/ቤት ህንፃ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የዲዛይን ስራውን በነፃ ሰርቶ አስረክቧቸው እንደነበር ተናገረዋል፡፡ ወደፊትም በወረዳው ለሚገኙ የሳይንስ፣የእንግሊዝኛ ቋንቋ እና ለሒሳብ መምህራን አጫጭር የስልጠና እድሎችን በመጠቀም እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው በሚያደርጋቸው ችግር ፈች ምርምሮችና የማህበረሰብ አገልግሎቶች የወረዳውን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ተቀናጅቶ ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልፀዋል፡፡

