የፋሲለደስ አጠ/2ኛ ደረጃ መሠ/ት/ቤትን ሞዴል ለማድረግ የተቋቋመው የኮምፒዩተር ማዕከል በይፋ ተመረቀ
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፋሲለደስ አጠ/2ኛ ደረጃ መሠ/ት/ቤትን ሞዴል ለማድረግ ያቋቋመው ሶስት የኮምፒዩተር ማዕከል ህዳር 28/2010 ዓ.ም በደመቀ ሁኔታ ተመረቀ ፡፡ በምረቃ ስነ ስርዓቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት፣ም/ፕሬዚዳንቶችና ዳይሬክተሮች እንዲሁም የጎንደር ከተማ አስ/ትምህርት መምሪያ ኃላፊ፣ የፋሲለደስ አጠ/2ኛ ደረጃ መሠ/ት/ቤት መምህራንና ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡
በምረቃ ስነስርዓቱ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የትም/ቤቱ ር/መ/ር ፣አቶ እንዳለ ታደሰ፣ እንደገለጹት እስከዛሬ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ኮምፒዩተር የሚጠቀሙት አንድ ለስድስት በመሆኑ የትምህርት ቤቱን አይ ሲ ቲ መርሀ ግብር ለመተግበር አስቸጋሪ ሁኔታ ነበር፡፡ ስለሆነም ዩኒቨርሲቲው ባደረገው ድጋፍ መሰረት ተጨማሪ ሶስት የኮምፒዩተር ማዕከላት በመዘጋጀታቸው ከዛሬ ጀምሮ የአይ ሲ ቲን ትምህርት ለማስተማር የተሻለና ምቹ ሁኔታ እንደሚኖር ርዕሰ መምህሩ እምነታቸውን ገልፀው ተጨማሪ የዩኒቨርሲቲው ድጋፍ እንዳይለያቸው አሳስበዋል ፡፡
የምረቃ ስነ ስርዓቱን በንግግር የከፈቱት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፣ ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ፣እንደተናገሩት የትምህርት ጥራትን ከፍ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው በርካታ ስራዎችን እየሰራ ነው፡፡ለአብነትም እርሳቸው በተማሩበት በፋሲለደስ የከፍተኛ ትምህርት መሰ/ት ቤት ከዚህ በፊት ለተወሰኑ መምህራን ነጻ የትምህርት እድል መስጠቱን አስታውሰው የትምህርት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግም አንድ መቶ ኮሚፒዩተሮችን የያዙ ሶስት የኮምፒዩተር ማዕከሎች ተዘጋጅተው ለትም/ቤቱ መሰጠታቸውን ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም የጎንደር ከተማ አስ/ትምህርት መምሪያ ኃላፊ፣ አቶ አቶ አማረ መስፍን፣ ዩኒቨርሲቲው ለዚህ ጥንታዊ የትምህርት ተቋም ባለፈው አመት፣ አንድ ድጅታል የኮምፒዩተር ማዕከል አቋቁሞ መስጠቱን አስታውሰው ፣ዛሬም ሶስት የኮምፒዩተር ማዕከላት በትምህርት ቤቱ በማቋቋም ይህን ትምህርት ቤት የልህቀት ማዕከል ለማድረግ የኮምፒዩተር ላብ ማዕከል በመክፈቱ በከተማ አስተዳደሩ ስም ትልቅ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በደስታው ዋኘው
የህ/ዓ/አ/ግ/ዳይሬክቶሬት

