ጉዞ፡ ቋራ – መቅደላ
ምንጊዜም ዝናቸውና ተምሳሌትነታቸው እየደመቀና እየገነነ በመሄድ ላይ የሚገኘው በአለም ስማቸው ካሳ ሀይሉ፣ በጦር ስማቸው መይሳው ካሳ፣ በፈረስ ስማቸው አባ ታጠቅ፣ በንግስና ስማቸው ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ፣ በ2000 ዓ.ም ደግሞ የምዕተ-ዓመቱ ጀግና ተብለው የተሰየሙት ባለ ሹርባው ቋረኛው ቴዲ የዛሬ 150 ዓመት መቅደላ አምባ ላይ ራሳቸውን ለሀገር አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡
ይህንኑ ምክንያት በማድረግ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሰቲዎች በጋራ በመሆን የ150ኛ ዓመት ዝክረ – ሰማዕት ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች ማለትም በጉዞ፣ ጥናታዊ ጹሁፍ በማቅረብ እንዲሁም በባህልና መዝናኛ ዘርፎች እንደሚከበር መገለጹ ይታወሳል፡፡ በመሆኑም የታሪክና ቅርስ ሙህራንንና ተማሪዎችን፣ የሚዲያ ሰዎችን እንዲሁም የሚመለከታቸው ሌሎች አጋር አካላትን ያካተተ የጉዞ ሉዓካን ቡድን የዳግማዊ አጼ ቴወድሮስ አሻራ ያረፈባቸውን ታሪካዊ ቦታዎችና ቅርሶች ከመጋቢት 12 – 18/2010 ዓ.ም ጎብኝቷል፡፡
[widgetkit id=8776]
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ም/ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ – ሰብዕ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ካሳሁን ተገኝ፣ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ት/ት ክፍል መምህራንና ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች እንግዶችን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ተቀብለዋል፡፡ ዶ/ር ደሳለኝ ስለዝግጅቱ ዓለማ በተደጋጋሚ መገለጹን አውስተዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ የዳግማዊ አጼ ቴወድሮስ ታሪክ የቅርብ ጊዜ ታሪክ መሆኑን ጠቁመው ነገር ግን ወደ አፈ ታሪክነት እዳይቀየር ለማድረግ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ይንን የመታሰቢያ ዝግጅት ማዘጋጁትን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ሁሉም የጉዞ አባላት በተለይም የሚዲያ ሰዎችና የታሪክ ሙህራን የአጼውን ታሪክ በሚገባ በመዘገብና በመሰነድ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ዶ/ር ደሳለኝ አሳስበዋል፡፡
ጉዞው በመኪናና በእግር የተደረገ ሲሆን በጉዞው አጼው የተወለዱበት ቋራ፣ መንፈሳዊ ትምህርት የተማሩበት ደምቢያ/ቸር ገር ተክለሀይማኖት/፣ የንግስና ክብራቸውን ያገኙበትን ጃን አሞራ/ደረስጌ ማርያም/፣ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የቴክኖሎጂ ስራ የጀመሩበትን ደ/ታቦር ጋፋት በመጨረሻም እራሳቸውን መስዋት ያደረጉበትን መቅደላ በአካል ተጎብኝተዋል፡፡ በደምቢያና በቋራ አካባቢ ከሚገኙ የአጼ ቴዎድሮስ የቅርብ ዘመዶችም ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ ከአንደኛው የታሪክ ምዕራፍ ወደ ሌላኛው የታሪክ ምዕራፍ እኛ ኢትዮጵውያን የተሻገርንበት ተብሎ የሚጠቀሰው፣ ቋረኛው ካሳ ሀይሉ/አባ ታጠቅ/ ከሽፍትነት ወደ ንጉሰ ነገስትነት ያደረጉት ጉዞ መሆኑ ይታወቃል፡፡ መሳፍንቱ በጎጥ ሸንሽኖና ተካፍሎ የማሽላ ዳቦ ያደረጋትን ሀገር እንደ ሉዓላዊ ሀገር እንዲኖረን በኩራት በየዘመኑ ለነበረው ትውልድና እኛም አሁን ላለንበት ማንነታችን የመጀመሪያውን መሰረት የጣሉና ይችን የምንሳሳላትን ትልቅ ሀገር ማገርና ምሰሶ ሆነው፣ ያገርን መደፈር ላለማየት የጉያቸውን ሽጉጥ ከአፎታቸው አውጥተው ለዚህ ታላቅ ህዝብና ሀገር መስዋትነት የከፈሉ ቃላት የማይገልጻቸው ታላቅ ዘመን የማይሽራቸው መሪ መሆናቸውን ብዙ የታሪክ ሙህራን ይስማማሉ፡
እኒህ ለ13 ዓመታት ብቻ በስልጣን ላይ የቆዩ ነገር ግን ተግባራቸው፣ ሀሳባቸውና አሻራቸው ከ150 ዓመታት በኋላ እንኳን ያልደበዘዘ በለራዕይ ጀግና አጼ ቴዎድሮስ የሰሯቸውን ስራዎችና የታሪክ አሻራዎችን ለመጎብኘት ከተጓዙ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ተማሪዎች ይገኙበታል፡፡ ስለጉብኝቱ ከጠየቅናቸው መካከል፣ የሶስተኛ ዓመት የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ት/ት ክፍል ተማሪ የሆኑትን ተማሪ ቤተል ሳምሶን እና ተማሪ ዮሴፍ አየነው ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡ ተማሪዎቹም የሀገር ፍቅር ማለት ምን ማለት እንደሆነ በተጓዙባቸው ቦታዎችና ባይዋቸው ቅርሶች ለመረዳት መቻላቸውን ተናግረዋል፤ ባጠቃላይ በጉብኝቱ እንደተደሰቱና ትምህርት አዘል ቁም ነገሮችን እንዳገኙ ገልጸዋል፡፡
በቋራ የሚገኙት ከአጼ ቴዎድሮስ ቅርብ ዘመድ አንዱ የሆኑት አቶ አወቀ እርስቱ ከአጼው ጋር ስላላቸው የዝምድና ሀረግ አብራርተዋል፤ መይሳው ካሳን የሚያወድስ ፉከራና ሽለላ አቅርበዋል፤ በመጨረሻም ወጣቱ ትውልድ የአጼ ቴዎድሮስን የሀገር ወዳድነት ስሜት በውስጡ አዋህዶ ለሀገር አንድነት የበኩሉን አስተዋፅኦ በመወጣት ለመጪው ትውልድ ማስረከብ እንደሚገባ አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
ስለ መይሳው ካሳ በመቅደላ 150 ዝክረ- ሰማዕት ዝግጅት ላይ የሚከናወኑ ተግባራትን እየተከታተልን የምንዘግብ ይሆናል፣ ለዛሬው በዚህ አበቃን፤ ቻው!!!
ዘገባ፡ አምሳሉ ግዛቸው
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

