ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከአጋር ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር እያደረገ ያለው የአይን ህክምና ዘመቻ በደልጊ የመ/ደ/ ሆስፒታል ላይ ተሰጠ
አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት አይኖቻችን እጆቻችን መሰራት ማይችሏቸውን እንድ ሺ ያህል ተግባራት ማከናወን ይችላሉ፡፡ ኢራናውያን አይኖች የልብ መመልቻ መስኮቶች ናቸው ይላሉ ምክንያታቸውም የአንድን ሰው ውስጣዊ ስሜት ማለትም መደሰት መከፋት ፣መስማማት መቃወም፣ታማኝ መሆንም ሆነ እምነት ማጉደል ለማወቅ አይኑን መመልት በግልጽ ያሳያል ሲሉ ነው፡፡
እንዲሁም አይኖቻችን ውበቶቻችን ከመሆናቸው በበለጠ የመላ አካላችን ብርሀኖች ናቸው ፡፡ ከሰወች ጋር በቀላሉ መግባባት ፣ እንደልብ ተንቀሳቅሶ የእለት ከእለት ህይዎትን መምራት ያለ አይን ብርሀን የማይታሰብ ነው፡፡ ታዲያ ይህን የመላ አካላችን ብርሀን የሆነውን አይናችን ከተለያዩ ጉዳቶች መጠበቅ ግድ የሚለን ጉዳይ ነው፡፡አንዳንድ የአይን ጉዳቶች ቶሎ ከታከሙ በቀላሉ መዳን የሚችሉ ናቸው፡፡በአለም ላይ ለአነስውርነት ከሚዳርጉ ምክንያቶች መካከል 50 በመቶ የሚሆነውን የሚይዘው የአይን ሞራ ግርዶሽ እንደሆነ በቅርቡ በአለም ጤና ድርጅት የተሰራ አንድ ጥናት ይጠቁማል፡፡ሆኖም ይህን የአይን ሞራ ግርዶሽም ሆነ ሌሎች ተዛማጅ በሽታዎችን በማከም ተጎጅ የሆኑትን በርካታ ሰዎች ብርሀን የመመለስና ከህመማቸው የመፈወስ ስራ በስፋት እየተሰራ ነው፡፡ ለአብነትም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከአጋር ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር በመሆን በተለያዩ አካባቢዎች የአይን ህክምና ዘመቻ እያካሄደ ይገኛል፡፡ በቅርቡም ከሚያዝያ 08/2010ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀናት በደልጊ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ህክምናው በዘመቻ መልክ ተሰጥቷል፡፡
[widgetkit id=9007]
በዚህም ስራ የበርካታ ሰዎችን የአይን ብርሃን መመለስና ከህመማቸው መፈወስ ተችሏል :: በአይን ሞራ ግርዶሽ ምክንያት ሁለት አይኖቻቸው ማየት ተስኗቸው በመሪ የመጡ አረጋዊያን ብርሃናቸው ተመልሶላቸው እያዩ ሄደዋል፤ ከትምህርት ገበታቸው ተለይተው የነበሩ ልጆች ማየት በመቻላቸው ደስታቸውን መቆጣጠር ሲያቅታቸው ታይተዋል፤በአይን ጸጉር መቀልበስ ምክንያት ለማየት ሲቸገሩ የነበሩ በርካታ ወገኖችም ከህመማቸው አገግመዋል፡፡
ቄስ ብልሃቱ ቸኮለ በፀጉር መቀልበስ ምክንያት ለብዙ ጊዜያት ለማየት ሲቸገሩ የቆዩ የአካባቢው ነዋሪ ናቸው፡፡ “ከቤታችን አጠገብ መጥቶ የአይን ብርሃናችንን ሚመልስልን ሲገኝ ምን እናመካኛለን? አይነስውሩ ሁሉ ይኸው አይኑ ቦግ አለ አይደል! በእውነት ይህን ያደረጉልን በምድር አይደለም በሰማይ ነው ሚጠቀሙ፣” በማለት ምስጋናና ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡ “በተደረገልኝ የአይን ህክምና እሔው ሳልቸገር ማየት ቻልኩ” ብለዋልም፡፡
መ/ጌታ ቀፀላ ከአለፋ እሰይ ደብር አካባቢ የመጡ ሌላው ታካሚ ናቸው፡፡ መ/ጌታ ቀፀላ ስለ ህክምና አሰጣጡ የተሰማቸውን ደስታ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፣ “የተሰራልኝ ሁለት አይኔን ነው ፤ ህመሙ ካስቸገረኝ ከሶስት አመት በላይ ይሆናል፤ባህርዳር ሄጀ ለመታከም ነገ ዛሬ ስል ህክምናው በቅርብ ከዚህ ድረስ መሰጠቱን ስሰማ መጣሁ፤ እንዲህ ያለ የለም፤ ህመም የለው በሽቦ አይታሰር፣እንግዲህ ምን እንላለን እያመሰገን ወደ ቤታችን ከመሄድ ውጭ፡፡”
ወ/ሮ ንግስቴ አታለለ፣ “በመሪ ነበር ወደ ህክምናው የመጣሁ አሁን ግን ሁለት አይኔን ታክሜ ጥሩ ለውጥ አግንቻለሁ” ብለዋል፡፡ ሌላኛዋ ታካሚ ወ/ሮ ፍርኑስ ፈረደ ደግሞ፣ “አንደኛው አይኔ ፈጽሞ አያይም ሌላኛውም ቢሆን በጸጉር ምክንያት ለማየት እየተቸገርኩ ነበርኩ አሁን ግን ሁለቱን አይኔን ታክሜ በመዳኔ ደስታ ተሰምቶኛል፣” በማለት ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡
የደልጊ የመጀመሪያ ደረጃ ሆሰፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ታደለ ሙሌ ፣ የአይን ህክምና ዘመቻ ቅስቀሳውን ለደልጊና አጎራባች ወረዳዎች ህብረተሰብ ለማድረስ ሀይማኖታዊ ተቋማትን፣ት/ቤቶችንና የመንግስት አደረጃጀቶችን መጠቀማቸውን ገልጸዋል፡፡ ስለሆነም ቅስቀሳው በስፋት ሰለተሰራ መታከም የሚገባው የህብረተሰብ ክፍል በቅስቀሳ ማነስ ምክንያት አለመቅረቱንና በቂ ታካሚ መታከሙን አብራርተዋል፡፡ አቶ ታደለ አያይዘውም ደልጊ የመ/ደ/ሆስፒታል በይፋ ስራ ሲጀምር ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመድሀኒትና የህክምና መገልገያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው ለህክምና ዘመቻው መሳካት አስተዋጽኦ ለአደረጉ ጎንደር ዩኒቨርሲቲና አጋር ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህክምና ቡድን አባላት እና ሌሎች አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በህክምናው ለበርካታ ሰዎች የአይን መድሀኒት ህክምና የተሰጠ ሲሆን በተለይ ለ149 ሰዎች የአይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገና ፣ለ34 ሰዎች የመነጽር ልኬታና እደላ እንዲሁም ለ84 ሰዎች የአይን ጸጉር መቀልበስ ቀዶ ጥገና እንደተደረገላቸው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ግብረሰናይ ድርጅት አስተባባሪ አቶ ሰማልኝ አበው ገልጸዋል፡፡
ህክምናውን ላልደረሳቸው አካባቢዎች በማድረስ በኩል ከጎንደር ዩኒቨርሲቲና ሌሎች አጋር ግብረሰናይ ድርጅቶች ማለትም “ላይት ፎር ዘ ወርልድ፣ካርተር ሴንተር፣ሶሊል ዲ አፍሪካ ፣ ሂማሊያን ካታራክትና ቪዥን ኦቨር ሲስ” ጋር በመተባበር የአማራን ክልል ማህበረሰብ እያገለገሉ መሆናቸውን ገልጸው በቀጣይ ዘመቻውን በሌሎች ክልሎች ለማካሄድ መታሰቡን አቶ ሰማልኝ አብራርተዋል፡፡ ህክምናው በዋናነት የሚያተኩረው የአይን ሞራ ግርዶሽና የአይን ጸጉር መቀልበስ ቀዶ ጥገና እንዲሁም የእይታ ማስተካካያ መነጽር እደላ ላይ መሆኑንም አስተባባሪው አያይዘው ገልጸዋል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህ/ጤ/ሳ/ኮ/ የአይን ህክምና መምህርና በአይን ሞራ ግርዶሽና የአይን ብሌን ንቅለ ተከላ ልዩ ስፔሻሊስት ዶ/ር ወሰን ሙሉጌታ ለህክምና ወደ ደልጊ የዘመተው ቡድን መሪ ናቸው፡፡ በቅርቡ ባሳተሙት የአይን ሞራ ግርዶሽና ህክምናው በሚል መጻህፋቸው የምናውቃቸው ዶ/ር ወሰን፣ በዘመቻው “በተለይ በአይን ሞራ ግርዶሽ የተሰጠው ቀዶ ጥገና ውጤታማ ስለነበር እንደ አንድ ዜጋና ሀኪም ደስታ ይሰማኛል፣” ብለዋል፡፡ በሶስት ቀናት ውስጥ ለበርካታ ሰዎች የአይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገና ከህጻናት እስከ ሽማግሌዎች መሰራቱን የገለጹት ዶ/ር ወሰን ከታካሚዎቹ መካከል ለብዙ አመታት ሙሉ በሙሉ አይነ ስውር ሆነው ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ ተስኗቸው የነበሩ ወገኖች ብርሃናቸው ተመልሶላቸው ያለ መሪ መንቀሳቀስ እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡
በደስታው ዋኘው
የህ/አ/አ/ግ/ዳይሬክቶሬት

