ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን የቱሪስት መስህብነት ለማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ፅ/ቤትና “አፍሪካን ዋይልድ ላይፍ ፋውንዴሽን “ጋር በመተባበር የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን የቱሪስት መስህብነት ለማሻሻል ትኩረት ያደረገ የአቅም ግንባታ ስልጠና ለአስጎብኞች እየሰጠ ይገኛል።
ዩኒቨርሲቲው ሀያ ለሚሆኑ አስጎብኝዎች(Tour Guides) ለአስራ አምስት ተከታታይ ቀናት የንድፈሀሳብና የተግባር ስልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴክኖሎጅ ሽግግር ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ቢኒያም ጫቅሉ ገልፀዋል።የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ትልቅ የሀገር ሀብት ነው፤ይህን ሀብት የበለጠ ለማስተዋወቅ አስጎብኝዎች የሚኖራቸው የታሪክ እውቀት በቂ ስለማይሆን ከአካባቢው የመሬት አቀማመጥ ፣ከተፈጥሮና እንስሳት ሀብት ጋር በተያያዘ ሳይንሳዊ የሆነ ግንዛቤያቸውን ለማስፋት አላማ በማድረግ ስልጠናው መሰጠቱን ተናግረዋል ።ይህንንም ተግባር ከአማራ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ጋር በመተባበር የበለጠ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።
በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የቱሪዝም ፍሰቱ በመቀነሱ ከፓርኩ ጋር በተያያዘ በተለያየ ስራ የተሰማሩ ሰራተኞች
ለኢኮኖሚ ችግር እንደተዳረጉ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ፈንታው አንስተዋል፤ይህ ስልጠና መሰጠቱም የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃትና ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ ወሳኝ እንደሆነ ገልፀዋል።
ከዚህ በፊት የአካባቢውን የተፈጥሮ ሀብት ለመጠበቅና የቱሪስት መስህብነቱን ለማሻሻል ዩኒቨርሲቲው በርካታ ስራዎችን እንደሰራም አስታውሰዋል።
የአሁኑ ስልጠና እየተሰጠ የሚገኘው የአስጎብኝዎችን አቅም ያሻሽላሉ በተባሉ መሠረታዊ ነጥቦች ላይ እንደሆነም አብራርተዋል።
በተለያየ ምክንያት ከአካባቢው እየሸሹ የሚገኙ እንስሳት ለምን እንደሚሸሹና የሚመለሱበትን መንገድ በተመለከተም የተለያዩ አካላትን ያሳተፈ ጥናት እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል።
ስልጠናውን እየሰጡ ከሚገኙት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህራን መካከል የጅኦሎጅ መምህር የሆኑት አቶ ውለታው አንዱአለም በፓርኩ የሚገኙ የመሬት ቅርፆች እንዴት እንደተፈጠሩ ሳይንሳዊ የሆነ የንድፈሀሳብና የተግባር ስልጠና እየሰጡ መሆናቸውን ገልፀዋል፤ይህም የጎብኝዎችን ፍላጎት በማርካት ለረዥም ጊዜ እንዲቆዩ ያግዛል ብለዋል።
በፓርኩ ውስጥ የተለያዩ ብርቅየ እንስሳትና አእዋፍ እንዳሉ ቢታወቅም የብዛ ህይወቱ መረጃ በበቂ ሁኔታ አልተጠናም እንዲሁም ለጉብኝት አልበቃም
።ስለሆነም አካባቢው ትልቅ የጥናት ምንጭ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የግብርናና አካባቢ ሳይንስ መምህር አቶ ጌታሁን ጣሰው በበኩላቸው ከፍታ በጨመረ ቁጥር ውስንና ብርቅ የሆኑ እፅዋትን እንደምናገኝ አብራርተዋል፤ በፓርኩ 1200 የሚሆኑ የእፅዋት ዝርያ እንደሚገኙ ቢገመትም እስከአሁን በዝርዝር የተቀመጡት ግን አምስት መቶ ገደማ የሚሆኑት ብቻ ገልፀዋል።ይህም የጥናት ክፍተት መኖሩን ያሳያል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው በምርምር ዘርፍ፣የማህበረሰቡንና የባለሙያዎችን ግንዛቤ በማስፋት፣በፓርኩ አካባቢ የሚከሰቱ ችግሮችን በመከላከል የሚያደርገውን አስተዋፅኦ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ
አቶ አዛናው ከፍያለው አድንቀዋል።የፓርኩን የቱሪስት መስህብነት ለመመለስ በሚያስፈልጉ የምርምር ፣የመሰረተ ልማት እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዩኒቨርሲቲውና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
ስለፓርኩ አመሰራረት ታሪክና በፓርኩ ውስጥ ስለሚገኙ እንስሳት፣አእዋፍ፣አለቶችና የመሬት አቀማመጥ ቅርፅ ሳይንሳዊ በሆነ የንድፈሀሳብና የተግባር ስልጠና መውሰዳቸውን የስልጠናው ተሳታፊ አስጎብኝዎች ገልፀዋል፤ከዚህ በፊት በፓርኩ ስለነበረው አጠቃላይ ብዛ ህይወት የነበራቸው ግንዛቤ አነስተኛና አዳዲስ የጥናት ውጤቶችን መሠረት ያላደረገ እንደነበር አንስተዋል፤ የአሁኑ ስልጠና ከአዳዲስ የጥናት ውጤቶች ጋር እንዲተዋወቁና ግንዛቤያቸው እንዲሰፋ እንደሚያግዝ ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲውን አመስግነዋል።
የንድፈሀሳብ ስልጠናው ለ13 ተከታታይ ቀናት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሲሰጥ መሰንበቱ ይታወቃል፤ በቀሪዎቹ ሁለት ቀናት ማለትም ግንቦት 13 እና 14/2015 ዓ.ም ፓርኩ ላይ በመገኘት ለአስጎብኝዎች በተግባር የተደገፈ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።
በነበረው የኮቪድና የሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ፓርኩን ለመጎብኘት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያልፉም በአሁኑ ሁኔታ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ለጎብኝዎች ክፍትና ሰላም በመሆኑ ሰልጣኞች፣አሰልጣኞችና የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ቦታው ድረስ በመሔድ ጎብኝተዋል።