35ኛው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማዊ ለውጥ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ተካሄደ
የሁለተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች ተብለው ከሚታወቁት 10 ዩኒቨርሲቲዎች በ2002 ዓ.ም የተመሰረተው የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ አቅሙን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጎለበተ በመምጣቱ 35ኛውን የከፍተኛ ተቋማዊ ለውጥ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ መርሃ ግብር እንዲያካሂድ በመመረጡ በዚሁ ዩኒቨርሲቲ ከጥቅምት 06 እስከ ጥቅምት 07/2010 ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉባኤ ተካሂዷል፡፡
ጉባኤው የተጀመረው በቤን ሻንጉል ጉሙዝ ክልል የቀይ መስቀል ሙዚቃ ባንድ አባላት ወጣቶች ባቀረቡት ውዝዋዜና መዝሙር ሲሆን ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የትምህርት ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ዶ/ር ሣሙኤል ክፍሌ ናቸው፡፡ ዶ/ር ሣሙኤል እንደገለጹት በሀገራችን የተጀመረውን የልማት፣ የሠላምና የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መደገፍ የሚችሉ ብቁ ሙያተኞችን ማፍራት ዓላማ ያለው የትምህርት ዘርፉ ሥራ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ሰፊና እመርታዊ ለውጥ አስመዝግቧል ብለዋል፡፡ እየተተገበረ የሚገኘው በ5ኛው የትምህርት ሴክተር ልማት ፕሮግራም የትምህርት ዘርፉን ተገቢነት በማረጋገጥ፣ ትምህርትና ስልጠናን ከልማት ጋር በማስተሳሰር ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ይሰጥ ዘንድ በመስፋፋት ውስጥ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የጥራት መጓደል ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን አዳዲስ ተግባራትን በመፈጸም ላይ መሆናቸውንም በመክፈቻ ንግግራቸው ገልጸዋል፡፡
የተከታታይ ምዘና/ Continuous assessment/ ትግበራ ላይ ያሉ ክፍተቶችና የመፍትሄ ሃሳቦች፣ የሥርዓተ ትምህርት ክምችት ፍኖተ- ካርታ፣ የሥርዓተ-ትምህርት ውይይት ውሳኔ ነጥቦች፣ የማሻሻያ ሐሳቦች፣ የጥራት ማስጠበቂያ ውስጣዊ አደረጃጀትና አሰራሮች በጉባኤው የቀረቡ ዋናዋና ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው፡፡
በጉባኤው ተሞክሯቸውን በሪፖርት እንዲያቀርቡ እድል ከተሰጡት ዩኒቨርሲቲዎች የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቀዳሚው ሲሆን የትምህርት ጥራትን በተመለከተ ገላጭ ሪፖርት ካቀረበ በኋላ በቤቱ ከፍተኛ ውይይትና ልምድ ልውውጥ ተደርጓል፡፡
በመጨረሻም የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ በተገኙበት ከ1ኛ እስከ 3ኛ ትውልድ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች በ13 ዋናዋና እና በ92 ዝርዝር መስፈርቶች በየዘርፋቸው በደረጃ ተለይተው ቀርበዋል፡፡ ደረጃውን አስመልክቶ ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ መሪ ቢኖርም ባይኖርም ራሱን ያደላደለ ዩኒቨርሲቲ ማየት እንደተቻለና በአንፃሩ ደግሞ ከነበረበት ደረጃ እየወርደ የመጣ ዩኒቨርሲቲ መኖሩን ገልጸዋል፡፡ ተባብሮ በመስራትና ለውጥ በማምጣት በአርዓያነት የሚጠቀሰው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በተያያዘ ከጥቅምት 09 እሰከ ጥቅምት 10/2010ዓ.ም በአሶሳ ከተማ ምክር ቤት አዳራሽ 27ኛው የከፍተኛ ትምህርት ለውጥ መደበኛ ጉባኤ ተካሂዷል፡፡ በጉባኤው የት/ት ማጭበርበር፣ የመምህራን ፍልሰት፣ የበጀት አጠቃቀምና የትምህርት ተከታታይ ምዘና በሰፊው የተነሱ ጉዳዮች ናቸው፡፡ የትምህርት ሚኒስትሩ በመሩት በዚህ ጉባኤ ላይ ሰፊና አከራካሪ ሀሳቦች የተነሱ ቢሆንም መግባባት ላይ በመድረሱ በቀጣይ የ2010ዓ.ም ተግባራትን በቁርጠኝነት ለመፈጸም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የቴክኒክና ሙያና የ2ኛ ደረጃ ትም/ቤት መሪዎች ከትምህርትት ሚኒስቴር ጋር የተግባራት ማስፈጸሚያ ውል ከተፈራረሙ በኋላ የዋንጫና የምስክር ወረቀት ሽልማት ተካሂዷል፡፡ በዚህ የሽልማት ፕሮግራም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ አፈጻጸም ከመጀመሪያው ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች 1ኛ በመውጣት የዋንጫና የምስክር ወረቀት ተሸላሚ ሆኗል፡፡ በተጨማሪም ከጥቅምት 13 እስከ ጥቅምት 15/2010 በተካሄደው አጠቃላይ የትምህርት ጥራት ግምገማ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 1ኛ በመውጣት በብሔራዊ ቤተ-መንግስት ከኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ከዶ/ር ሙላቱ ተሾመ እጅ የዋንጫና የምስክር ወረቀት ተረክቧል፡፡
የሁለቱንም ድርብ ድሎች ማብሰሪያ የድል ዋንጫዎች የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻና የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሥራት ዓፀደወይን የመሩት የልዑካን ቡድን ጎንደር ሲገባ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ከዓፄ ቴዎድሮስ ግቢ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት ደማቅ አቀባበል አድርገውለታል፡፡
ዘጋቢ፡- በላይ መስፍን
ኤዲተር፡-ደምሴ ደስታ
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት