የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 1ኛ ወጣ
የጎንደር ዩኒቨርቲ በሀገሪቱ ከሚገኙ ነባር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተወዳድሮ በ2008 በጀት ዓመት አጠቃላይ አፈፃፀም 1ኛ በመውጣቱ የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል፡፡
የሽልማት ዋንጫዉን ይዘዉ የመጡት የዩኒቨርሲቲው የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ እና የመንግስት ፋይናንስ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክቶር ዶ/ር ስንታየሁ ወ/ሚካኤል፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን ሲሆኑ ህዳር 10/2009 ዓ.ም ወደ ጎንደር ሲገቡ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

በአቀባበል ስነ-ስርዓቱ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ፣ የሰሜን ጎንደር ዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ የጎንደር ከተማ አስተዳደር እና የየክፈለ ከተማ ማህበረሰብ ተወካዮች፣ የፋሲል ከነማ የእግር ኳስ ቡድን የደጋፊ ማህበር ተወካዮች አንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በጋራ በርከት ያሉ በዩኒቨርሲቲው አርማ ያሸበረቁ መኪናዎችን በመጠቀም ጎንደር አፄ ቴዎድሮስ አየር ማረፊያ ድረስ በመሄድ ዋንጫውን ይዘው ለመጡ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች በዓይነቱ ደማቅ የሆነና ቀልብን የሚስብ አቀባበል አድርገዉላቸዋል፡፡ በመቀጠልም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሶስቱ ግቢዎች ማለትም፣ አፄ ፋሲል፣ አፄ ቴዎድሮስ እና ማራኪ ግቢዎችን በማዳረስ እና ለየግቢው ማህበረሰብ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ዋናው የአቀባበል ዝግጅት ወደ ሚካሄድበት ሳይንስ አምባ አዳራሽ አምርተዋል፡፡

በሳይንስ አምባ አዳራሽ የአቀባበል ዝግጅት ላይ የእንኳን ደስ አላችሁ እና የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ም/ፕዚዳንት ዶ/ር ታከለ ታደሰ አድርገዋል፡፡ በንግግራቸውም የዩኒቨርሲቲው ሁሉም ማህበረሰብ ማለትም ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ባለሙያዎች እና አመራሮች ቀና የሆነ አመለካከት እና የስራ ተነሳሽነት ዩኒቨርሲቲው ለዚህ የላቀ ውጤት እንዲበቃ አድርጎታል ብለዋል፡፡
በመቀጠልም ዶ/ር ስንታየዉ ወ/ሚካኤል የዩኒቨርሲቲው የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ እና የመንግስት ፋይናንስ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው የተሰጠውን ተልዕኮ ባለፉት ዓመታት በብቃት፣ በጥራት እና በቅልጥፍና ሲያከናውን በመቆየቱ በተከታታይ ዓመታት ዩኒቨርሲቲውን በደረጃ ውስጥ እንዲቆይ አድርጎታል፡፤ በመሆኑም በ2008 ዓ.ም ጠንክሮ በመስራት የደረጃው ቁንጮ ላይ እንዲገኝ አብቅቶታል፡፡ ለዚህም ውጤት |የሁሉም የዩኒቨርሲቲዉ ማህበረብ አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነዉ ብለዋል፡፡ አክለውም ይህን የተገኘውን ውጤት በላቀ ደረጃ በማስቀጠል እና በማረጋገጥ ውድድሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ አልፎ አለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ዩኒቨርሲቲው ባገኘው ሽልማት ዙሪያ እና ምን አይነት አንኳር የዩኒቨርሲቲው ተግባሮች ለሽልማት እንዳበቁት በርከት ያሉ ነጥቦችን ዘርዝረዋል፡፡ ለአብነት ያህል ዶ/ር ደሳለኝ እንዳሉት ውጤቱ በዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራት ድምር ዉጤት መሆኑን ገልፀዉ አሁን ያለበት የአንደኝነት ደረጃ እንዲያዝም አመራሮችና ሰራተኞች የበኩላቸውን ድርሻ መወጣታቸው፣ ዩኒቨርሲቲው በጤናውና በሌሎች ዘርፎች የታወቁ ተመራማሪዎችንና ሙህራንን ማፍራትና እያፈራ ያለ ተቋም መሆኑ፡፡ በተጨማሪም የማህበረሰብ ችግሮችን ዩኒቨርሲቲው ሲፈታ መቆየቱና በመፍታት ላይ ያለ ተቋም በመሆኑ እና በሌሎች አበይነት ተግባራት ለሽልማት መብቃቱን ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰው በ2007 ዓ.ም በኢትዮጵያ የጥራት ድርጅት ዩኒቨርሲቲዉ የአንደኛ ደረጃ ተሸላሚም እንደነበር አውስተዋል፡፡

ፕረዝዳንቱ እንደገለፁት ውጤቱ በዋናነት የሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የጋራ ርብርብ በመሆኑና የተለያዩ አጋር አካላት ለውጤቱ አስተዋፆ ቀላል የማይባል አበርክቶ ያላቸው በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ ጋባዥነት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ እና ዶ/ር ስንታየሁ ወ/ሚካኤል ለዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲዉ ጋር በቅርበት ሲሰሩ ለነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የዕውቅና ሽልማት ሰጥተዋል፡፡
በዕለቱ በአቀባበል ዝግጅቱ ላይ የተገኙ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እና የተለያዩ አጋር አካላት የዩኒቨርሲቲው ደስታ ደስታቸው መሆኑን ገልፀው የዩኒቨርሲቲዉን የቀዳሚነት ደረጃም ለማስጠበቅ አብረው በጋራ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡

ዘጋቢ፡ አምሳሉ ግዛቸዉ
አርታኢ፡ ደስታዉ ዋኛዉ

