በእስር ቤት ቆይታ ጉዳት ለደረሰባቸው ግለሰቦች ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ተግባራት ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጠናክረው እየቀጠሉ ይገኛሉ፡፡ በምዕራብ፣ በማዕከላዊና በሰሜን ጎንደር ዞኖች ለሚገኙ በፖለቲካ እስር ቤቶች፣ በነጻነት ትግልና ተያያዥ ሁኔታዎች ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በአይነቱ ለየት ያለ ስልጠና በዩኒቨርሲቲው የህግ ት/ት ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ እየተሰጠ ይገኛል፡፡

በስራ ፈጠራ ጥበብ፣ ክህሎትና ብቃት እንዲሁም በስነ ልቦና ዙሪያ ስልጠናው ትኩረት ያደርጋል፤ ከዛሬ ታህሳስ 16/2012 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 5 ቀናት ቆይታ እንዳለውም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ በማሰልጠን በኩል ደግሞ በየዘርፎቹ ሰፊ ልምድ ያካበቱ የዩኒቨርሲቲው መምህራን ተሳትፎ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

ስለ ስራ ፈጠራ ጥበብ፣ ክህሎቶችና ባህርያት በሰልጣኞች ዘንድ ግንዛቤን መፍጠር፤ ተሳታፊዎች እንደ ቢዝነስ ባለሙያ ትክክለኛና አጠቃላይ የሆነ አቅማቸውን/እምቅ ኃይላቸውን እንዲፈትሹ ማድረግ እንዲሁም የባለድርሻ አካላትና ተቋማትን አመለካከት፣ እውቀትና ክህሎት በማደበር ለኢንተርፕርነርሽፕ ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲወጡ ማስቻል፣ የስልጠናው ዋና ዋና ዓላማወች መሆናቸውን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ጌታ አስራደ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ስልጠና ያልተሳተፉ ተመሳሳይ የህብረተሰብ ክፍሎች በቀጣይ ዙሮች መሰል ዕድል እንደሚያገኙ አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡ አቶ ጌታ አያይዘውም ከሎሌች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ሰልጣኞች በቀሪው የህይወት ዘመናቸው ወደ ስራ መሰማራት እንዲችሉ በማድረግ፣ ከማህበረሰቡ ጋር መልካም የኢኮኖሚአዊና ማህበራዊ መስተጋብር እንዲፈጥሩ ይደረጋል ብለዋል፡፡



