በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን በዘላቂነት ለማስቀጠል ከጎንደር ከተማ የተለያዮ ማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ተካሄደ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ዘላቂ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስፈን ዓላማ ያደረገ ውይይት ታህሳስ 20/2012 ዓ.ም ሀይሌ ሪዞርት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሄደ፡፡ በውይይቱ የጎንደር ከተማ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣የጎንደር ከተማ ሰላም እና ልማት ሸንጎ አባላት፣ ወጣቶች እንዲሁም የተለያዩ ማህበራት ሀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ውይይቱን ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አማካሪ የሆኑት ዶ/ር አለማየሁ ከበደ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን፣ ከአማራ ብልፅግና ፓርቲ አቶ ደሳለኝ በላቸው፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ክብርት ወ/ሮ አስናቀች ለገሰ እንዲሁም ከኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ አቶ ባህሩ አሸኔ መርተውታል፡፡

ለውይይቱ መነሻ የሚሆኑ ሀሳቦች በዶ/ር አለማየሁ ከበደና በዶ/ር አሥራት ዓፀደወይን የቀረበ ሲሆን፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ወቅታዊ ሁኔታ፣ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት የተወሰዱ ርምጃዎች፣ ቀሪ ስራዎችና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ሌሎች አጋር አካላት ላይ ወደፊት ስለሚጠበቅ ሚና ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የመነሻ ሀሳቡን ተከትሎም በተወያዮች በርካታ ሀሳቦች ተነስተው ውይይት ተካሂዷል፡፡

ከተነሱ ሀሳቦች መካከልም መንግስት ህግ የማስከበር ስራ ጠንክሮ መስራት አለበት፣ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል አመራሮች ተቀራርበው ለመፍትሄው መስራት አለባቸው፣ ከሌላ ክልል ትምህርታቸውን አቋርጠው ለመጡ የአማራ ክልል ተማሪዎች መፍትሔ ሊሰጣቸው ይገባል፣ ዩኒቨርሲቲው በውስጡ ያሉ ሠራተኞችን ሊፈትሽ እና ውስጣዊ ችግሮችን ሊፈታ ይገባል፣ ዩኒቨርሲቲው ጥበቃ እና ቁጥጥሩን የበለጠ ሊያጠናክር ይገባል፣ በየደረጃው ተከታታይ የሆኑ ውይይቶች መደረግ አለባቸው እንዲሁም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሀላፊነት ሊወጡ ይገባል የሚሉ ሀሳቦች ይገኙበታል፡፡



