በእስር ቤት ቆይታ ጉዳት ለደረሰባቸው ግለሰቦች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቀቀ፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ቢሮ በምዕራብ፣ በማዕከላዊና በሰሜን ጎንደር ዞኖች ለሚገኙ በነጻነት ተጋድሎ ምክንያት በፖለቲካ እስር ቤቶች ለቆዩ፣ ከስራ ተፈናቅለው ለነበሩና ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በአይነቱ ለየት ያለ ስልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ስልጠናዉ ከታህሳስ 15-21/2012 ዓ.ም ድረስ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማራኪ ካምፓስ በሚገኘው የህግ ት/ት ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ተሰጥቷል፡፡ በስነ-ልቦና ግንባታ፣ በስራ ፈጠራ፣ ራስን በመምራት ጥበብ፣ በቢዝነስ አሰራር እና እቅድ፣ በህይወት ክህሎት፣ በጊዜ አጠቃቀም እና በመሰል ጉዳዮች ስልጠናው ትኩረት አድርጓል፡፡ የፕሮጀክት አስተባባሪዎች እና አሰልጣኞች ስልጠናውን በመስጠት በኩል የነቃ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ የሆኑት ረ/ፕሮፌሰር ጌታ አስራደ እንደተናገሩት ስልጠናው በዚህ ዓመት በማዕከላዊ፣ በምዕራብና በሰሜን ጎንደር ለሚገኙ መሰል አካላት፣ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፏቸዉ እንዲነቃቁ ለማድረግ የታቀደ ነው ብለዋል፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ቀጣይ 3 ዙሮች መኖራቸውንም አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

ስልጠናው፣ ከዚህ በፊት ሰልጣኞች የደረሰባቸዉን ኢ-ፍታዊ ተግባራት እንዲረሱ ከማድረጉም በላይ ወደ ልማት እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸዉ እና በሀገራዊ የሰላም ግንባታ ሂደት የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ረ/ፕሮፌሰር ጌታ ገልጸዋል፡፡ አስተባባሪው አያይዘዉም ስልጠናዉን ለወሰዱ አካላት መነሻ የሚሆን የብድር እና የመስሪያ ሁኔታዎች (የስራ መስኮች) በመንግስት በኩል ሊመቻች እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህ/ጤ/ሳይንስ ኮሌጅ የምርምር፣ ማ/ሰብ አገልግሎትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ቢኒያም ጫቅሉ በስለጠናዉ መዝጊያ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት፣ ባለፈዉ ስርዓት በተፈጠረዉ የፍትህ ጥያቄ ላይ ከፍተኛ መስዋዕት ለከፈሉ አካላት በአቅም ግንባታ እና ህክምና ዙሪያ ድጋፍ ለማድረግ ታስቦ ይህ ፕሮጀክት እንደተፈቀደ ገልፀዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዉም ስልጠናዉን ከማሰልጠን ባሻገር ሰልጣኞቹ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሱ ክትትል እንደሚያደረግ እና ከልዩ ልዩ አጋር አካላት ጋር በትብብር ለመስራት እንዳሰበ ደ/ር ቢኒያም አያይዘው ገልጸዋል፡፡
ሰልጣኞች ከስልጠናው በርካታ ቁም ነገሮች እንደጨበጡ የገለጹ ሲሆን ወደ ስራ ለመግባትም ከፍተኛ መነቃቃት እንደተሰማቸውና ብሩህ የስራ መንፈስ እንደታያቸው ገልጸዋል፡፡



