(ፍና ተክሌ) የተክሌ መንገድ የሚል ትውፊታዊ ቴአትር ለእይታ ቀረበ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ የቲያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል #ፍና ተክሌ$ የተክሌ መንገድ የሚል ትውፊታዊ ቴአትር ጥር 7/2012 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው የቲያትር አዳራሽ ለእይታ ቀረበ፡፡

በዕለቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ካሳሁን ተገኘ፣የኮሌጁ ዲን ዶ/ር አገኘሁ ተስፋ፣ የሙሉአለም የባህል ማዕከል ስራ አስኪያጅ አቶ አየነው አዲስ፣ የኔታ ቀለመወርቅ፣መምህር ኃይለ እየሱስ ብርሀኑ ከደብረታቦር እየሱስ ገዳም፣መምህራን፣ተማሪዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ይህ #ፍና ተክሌ$ የተክሌ መንገድ የሚል ትውፊታዊ ቴአትር የ3ኛ አመት የቲያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ተማሪዎች የተሳተፉበት እና በተማሪ ሜሮን ወልዱ፣ ብዙነሽ አገኘሁ እና ሀብታሙ ደምለው የተደረሰና በመምህር ሙሉጌታ አበራ ዋና አዘጋጅነት የተሰራ ሲሆን፣ተማሪ ናትናኤል ዮሀንስ በረ/አዘጋጅነት ተሳትፈዋል፡፡

የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ አቶ አንተነህ ወርቅነህ በት/ት ክፍላቸው መምህራንና ተማሪዎች የተዘጋጀውን ቴአትር አስመልክቶ አስተያታቸውን የሰጡ ሲሆን በንግግራቸው ጎንደር የበርካታ ባህሎች የጥበብ ማህደር እንደሆነች፣ ከነዚህ የጥበብ ማህደሮች መካከል በአለቃ ገብረሐና ተደርሶ በልጃቸው በተክሌ የተሰየመው የተክሌ አቋቋም አንዱ መሆኑን አውስተው፣ ይህ ሀገር በቀል እውቀት በመጽሀፍም ሆነ በመቅረፀ ድምፅ ተቀርፆ ሳይቀመጥ ከመቶ አመት በላይ በቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሻገረ ዛሬ ላይ ቢደርስም ይህ የተክሌ አቋቋም ሀገር በቀል እውቀት ቀጭጮ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ አቶ አንተነህ አያይዘውም ይህ ትውፊታዊ ቴአትር ጥልቅ ጥናትና ምርምር በማድረግ የተሰራ፣ የዘርፉ ምሁራንን ያሳተፈ፣ የትምህርት ክፍሉን መምህራንና ተማሪዎች ኪናዊ ብቃት አሟጦ የተጠቀመ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም መምህር ኃይለ እየሱስ ብርሀኑ የተክሌ አቋቋምን በተመለከተ አጭር ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ ፅሁፉን እና የቀረበውን ቴአትር መነሻ በማድረግ ሀገር በቀል እውቀቱ አሁን ላይ የተጋረጠበትን ችግሮች እና መፍትሄ ሀሳብ አመላካች ምክረ ሀሳቦች የቀረቡበት ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡



