የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ለመቀነስ የሚያግዝ ስልጠና ተሰጠ
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ እና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ እና አቅም ግንባታ ለማጎልበት የሚያግዝ ስልጠና ጥር 08/2012 ዓ.ም በጠዳ ግቢ ሰጥቷል።

የስልጠናው አስተባባሪ አቶ አለምነው አበበ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው እንደገለፁት ስልጠናው በ2011 ዓ.ም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ባዘጋጀው የህፃናት ጉዳይ ማካተቻ መመሪያ መሰረት የተመረጡ 45 ተሳታፊዎች ከጎንደር ዙሪያ ወረዳ ከሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች፣ ከፍትህ አካላት፣ ከፖሊስ፣ ከሀይማኖት አባቶች፣ ከሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ፣ ከጤና፣ ከትምህራት ቤቶች እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተውጣጡ ሰልጣኞች እንደተካተቱ ተናግረዋል።
አቶ አለምነው አያይዘው እንደገለፁት የህፃናት የጉልበት ብዝበዛ ንድፈ-ሃሳቦች፣ ዓለም አቀፍ፣ ሀገራዊ እንዲሁም ክልላዊ ህጎች፣ የፖሊሲ ማዕቀፎች እንዲሁም የጉልበት ብዝበዛ በህፃናት ልጆች የሚያስከትለውን አካላዊ፣ ማህበራዊ እና ሞራላዊ አሉታዊ ተጽእኖ ባለድርሻ አካላት እንዲረዱ ማድረግ እና ከማን ምን ይጠበቃል የሚለውን በመለየት ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት የሚወስዱበት ስልጠና ነው ብለዋል።

የንደፈ ሃሳብ ስልጠናውን የሰጡት ዶ/ር ምሳየ ሙላቴ “የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ማለት ማንነትን (ስብዕናን) የሚጎዳ፣ አካላዊ እና አዕምሮኣዊ እድገት የሚገድብ፣ ማህበራዊና ሞራላዊ መጥፎ ጠባሳ የሚጥል እዲሁም ትምህርት እነዳይማሩ እና እንዳይከታተሉ የሚያደርጉ ማናቸውም ድርጊቶች ናቸው” ብለዋል። እንደ ዶ/ር ምሳየ ገለፃ የከፋ የጉልበት ብዝበዛ እየደረሰ ያለው ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት መሆኑን ጠቅሰው በኢትዮጵያ 16 ሚሊዮን በሚሆኑ እድሜአቸው ከ5-17 የሆኑ ህፃናት ልጆች የጉልበት ብዝበዛ እንደሚደርሱባቸው የሚያሳይ የጥናት ውጤት አቅርበዋል፡፡ የጉልበት ብዝበዛ የሚደርሰው በአብዛኛው በገጠሩ የሀገራችን ክፍል እንደሆነ እና ዋና የጉልበት ብዝበዛ የሚያካሂዱት ደግሞ ወላጆች ናቸው ሲሉ ዶ/ር ምሳየ ለሰልጣኞች ተናግረዋል። እንደአካባቢው ሁኔታ መጠኑ ይለያይ እንጂ በጎንደር እና አካባቢው ባሉ ወረዳዎች ለችግሩ ተጋላጭ እንደሆኑ የሚያሳይ የጥናት ውጤት በስልጠናው የቀረበ ሲሆን በግብርና አካባቢ 8.8%፣ በከብት ጥበቃ 19.4% እና በቀን ሰራተኝነት ደግሞ 18.3% ህፃናት ልጆች በከባድ ስራ እንደተሰማሩ ተመልክቷል።

የማህበራዊ እና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር መስፍን ደስየ በበኩላቸው “የህፃናትን ጉልበት ብዝበዛ ማስቀረት እንኳን ባንችል ችግሩን ለመቀነስ የእናንተ የባለድርሻ አካላት ርብርብ አስፈላጊ ነው” ብለዋል። እንደ አስተባባሪው ገለፃ ይህ ስልጠና ለሰልጣኞች ማንቂያ እና ማነሳሻ ሲሆን ሰፊ ቁጥር ወዳለው ማህበረሰብ በሚቀላቀሉበት ጊዜ የማስተማር እና ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ይሰራሉ ብለው እንደሚጠብቁ በንግግራቸው አውስተዋል።
ህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳሬክቶሬት



