የስራ ፈጠራ ጥበብ፣ የክህሎት እና ብቃት ማሳደጊያ ስልጠና ተሰጠ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤናሳይንስ ኮሌጅ የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪነት የስራ ፈጠራ ጥበብ፣ የክህሎት እና ብቃት ማሳደጊያ ስልጠና ከየካቲት 01-05/2012 ዓ.ም ተሰጠ፡፡

ስልጠናው በፖለቲካ አስር ቤት፣ በትጥቅ ትግል እና በመሰል ሁኔታዎች አካላዊ፣ ስነ ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት የደረሰባቸውን አካላት ወደ ቀደሞ ሁኔታቸው ለመመለስ ታስቦ በዙር ሲሰጥ የቆየ ስልጠና ነው፡፡ በዚህ ስልጠና የማጠናቀቂያ መርሀ ግብር ከዚህ ቀደም የተሰጡት ስልጠናዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ በሶስቱም ዙሮች የተሰጡት ስልጠናዎች ምን ያክል ውጤታማ ነበሩ፣ እነዚህን አካላት ወደ አምራች ሀይልነት ለመመለስ ከግለሰቦቹ፣ ከዩኒቨርሲቲውና ከማህበረሰቡ ምን ይጠበቃል በሚል ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ውይይቱን የመሩት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንትና የፕሬዚዳንቱ ተወካይ ዶ/ር ጋሻው አንዳርጌ እና የምርምር እና ህትመት ዳይሬክቴሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ዘውዱ ተሸመ በዩኒቨርሲቲው በኩል ሊሰጡ ስለሚችሉ ስልጠናዎችና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች አብራርተዋል፡፡ ከተሳታፊዎች ለተነሱ በርካታ ጥያቄዎችም ምላሽ የሰጡ ሲሆን ወደፊት ከከፍተኛ አመራሩ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር ለእነዚህን ተጎጅ አካላት ምቹ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ወደ አምራችነት ለመመለስ ዩኒቨረስቲው ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ ሌሎች በተመሳሳይ ሁኔታ ለነበሩ እና ይህንን መሰል የክህሎት ስልጠና ላልወወሰዱ አካላትም ስልጠናው እንዲሰጣቸውና ወደፊትም በጥናት በመታገዝ የራሳቸውን የገቢ ምንጭ የሚያገኙባቸውን ሁኔታዎች ለማመቻቸት ዩኒቨርሲቲው ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ የሆኑት ረ/ፕሮፌሰር ጌታ አስራደ ዩኒቨርሲቲው ፕሮጀክቱን ተቀብሎ ተግባራዊ እንዲሆን ለደረገው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ተሳታፊዎችም በበኩላቸው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከነበሩበት የስነ ልቦና ጫና እንዲወጡ እና ራሳቸውን ለመቀየር የሚያግዙ ብዙ ቁምነገሮች ከስልጠናው ማግኘታቸውን ገልፀው ለዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም ስልጠናውን በአግባቡ ለተከታተሉ ተሳታፊዎች የምስክር ወረቀት ተሰጥቶ የስልጠና መርሀግብሩ ተጠናቋል፡፡



