‹‹የአይን ብርሃንን ከመመለስ በላይ ምን የህሊና እርካታ ይገኛል›› ዶ/ር ሊያ ሰለሞን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአይን ህክምና ስፔሻሊስት
የጎንደር ዩኒከቨርሲቲ እና ታሪካዊ አመሰራረቱ ከማህበረሰብ ጤና አገልግሎት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ይታወሳል በመሆኑም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ የማህበረሰቡን ጤና ለመጠበቅ በሰሜን ጎንደር ዞን በየዳ ወረዳ ድል ይብዛ ከተማ ጤና ይስጥልን በማለት ጎራ ብሏል፡፡

የህመም ቀላልና ከባድ ባይኖረውም ‹‹የአይን ጉዳይ አይን›› በመሆኑ የተለየ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም የዩኒቨርሲቲው ህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከፍተኛ ሙያተኞች በድል ይብዛ ከተማ ከክፍያ ነጻ የሆነ የአይን ህክምና ዘመቻ ከየካቲት 9 እስከ 14/2012 ዓ.ም እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡

በዘመቻው የመድሃኒት ህክምና፣የአይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገና ህክምና፣የአይን ቆብ መቀልበስ ቀዶ ጥገና ህክምና እና የመነጽር ልኬታ እና እደላ አገልግሎቶች በመሰጠት ላይ ናቸው፡፡
የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚደንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ እና የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ፋንታውም በህክምና መስጫ ቦታው በመገኘት የህክምና ቡድኑን ስራ አበረታተዋል፡፡

የአይን ህክምና ዘመቻዎችን ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከአጋር ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሚያካሂድ ሲሆን በበየዳ ወረዳ በአሁኑ ዘመቻ ብቻ 400 የአይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና ስራዎች ለመስራት ታቅዷል፡፡
በ2012 ዓ.ም ግማሽ በጀት ዓመት በሰሜንና ደቡብ ጎንደር ዞኖች በሚገኙ አስር ወረዳዎች ተመሳሳይ ዘመቻዎች ሲካሄዱ የቆዩ ሲሆን በቀጣይም ወደ ሌሎች ዞኖች እና ወረዳዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አቶ ሰማልኝ አበው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኦርቢስ ኢንተርናሽናል አስተባባሪ ተናግረዋል፡፡

በዘመቻ ስራው ከ15 በላይ የህክምና ቡድን የተሳተፉበት ሲሆን የአይን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሊያ ሰለሞን በዘመቻው ከ98 በመቶ በላይ የአይን ሞራ ግርዶሽ ችግር እንደገጠማቸው ገልጸው በተለይም ለረጅም ጊዜያት የአይን ብርሃናቸውን አጥተው የነበሩ አባትና እናቶችን እይታ መመለስ መቻል ያለው እርካታ የላቀ መሆኑን ገልጸውልናል፡፡
በግማሽ በጀት ዓመቱ በተካሄዱ ዘመቻዎችም 52,000 አጠቃላይ የአይን ህክምና አገልግሎት የተሰጠ ሲሆን ከነዚህ መካከል 32,000 የመድሃኒት ህክምና፣994 የአይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና፣627 የአይን ቆብ መቀልበስ ቀዶ ህክምና፣25,217 የመነጽር ልኬታ ከነዚህ ውስጥ ለ5,297 ታካሚዎች መነጽር ታድሏል፡፡

የመንገድ መሰረተ ልማት ባልተሟላበት እና በቀላሉ የህክምና አገልግሎቶችን ማግኘት በማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት ለከፊል እና ሙሉ የአይን እይታ ችግር ተጋልጠው የነበሩ የህክምና አገልግሎቱ ተጠቃሚ የበየዳ ወረዳና አካባቢው ነዋሪዎች ዩኒቨርሲቲው ካሉበት አካባቢ ድረስ መጥቶ በነጻ አገልግሎቱን በመስጠቱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የታካሚዎች መነጽር እና ልዩ ልዩ የህክምና ግብዓቶችን በአብዛኛው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሚቀርብ ሲሆን አጋር አካላትም ለዘመቻዎች መሳካት ቀላል የማይባል ሚናን ተጫውተዋል፡፡



