የመስኖ ልማት ላይ ግንዛቤ ማስጨበጥን አላማው ያደረገ ስልጠና ተሰጠ
በበየዳና ጃናሞራ ወረዳዎች ያለውን የውሃ ሃብት በአግባቡ በመጠቀም በመስኖ ልማት የአርሶ አደሩን ህይወት በማሻሻል ላይ ትኩረት ያደረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በድል ይብዛ ከተማ በመሰጠት ላይ ነው፡፡

ስልጠናውን በዘርፉ በተለይም በሰሜን ጎንደር አካባቢ ባለው የውሃ ሃብት ላይ ግንዛቤ ያላቸው ምሁራን በመስጠት ላይ ሲሆኑ በተለይም በከፍታው ተጠቃሽ ከሆነው ራስ ደጀን ተራራ የሚመነጨውን የውሃ ሃብት ያለምንም ጥቅም እንዳይባክን እያንዳንዷን ጠብታ ለምርት በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያስችላል ተብሏል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕ/ር መርሻ ጫኔ ስልጠናውን በንግግር ሲከፍቱ እንደተናገሩት የአካባቢው ማህበረሰብ የሚያመርታቸው አዝዕርት ውስን ናቸው፤ነገር ግን በመስኖ አማካኝነት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የውሃ ሃብታቸውን በአግባቡ ቢጠቀሙ በርካታ አዝዕርትን በማምረት የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ማጋገጥ ይቻላል፡፡ስለሆነም ይህንን ለማድረግ ስልጠናው ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከዚህ በፊትም በእንስሳት ሃብት ልማት በተለይም በንብ ማነብ ዙሪያ ለአርብቶና አርሶ አደር የአካባቢው ነዋሪዎች ስልጠና የሰጠ መሆኑን ያስታወሱት የበየዳ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ታደገኝ ዩኒቨርሲቲው በትምህርት፣በጤና፣በቱሪዝም፣በህግ እና በግብርና ዘርፎች ከወረዳው ጋር በቅርበት መስራት መጀመሩን አድንቀው ለወደፊቱም በተለያዩ ዘርፎች ከዩኒቨርሲቲው ጋር ለመስራት ወረዳው ዝግጁ መሆኑን ለህዝብና አለማቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ገልጸዋል፡፡

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተደጋጋሚ በግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች አማካኝነት የተሻለ ህይወትን የሚመራ አምራች እና ምርቱም ለሃገር የሚበቃ አርሶ አደር ይኖር ዘንድ ከየአካባቢው ሁኔታ ጋር የሚዋሃዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን በተከታታይ ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል፡፡



