ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ
የማህበራዊ ሳይንስ እና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የሥነ-ዜጋ እና ሥነ-ምግባር ትምህርት ክፍል ለባለድርሻ አካላት እና ለድርጊቱ ሰለባ ለሆኑ ግለሰቦች በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ምንነት፣ መንስኤዎች እንዲሁም የሚያስከትለውን የሰብአዊ እና ስነልቦናዊ ቀውስ የሚያስገነዝብ ስልጠና ዛሬ የካቲት 20/2012 ዓ.ም በጠዳ ግቢ እየሰጠ ነው።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት “የዛሬው ስልጠና በሀገራችን በብዙ ተስፋፍቶ ያለ እና ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በሰዎች ላይ የሚያስከትለው ሰብአዊ እና ስነልቦናዊ ተፅእኖ ከፍተኛ በመሆኑ እና ችግሩ ደግሞ በተለይም በህፃናት እና ሴቶች ላይ የሚከሰት በመሆኑ ትኩረት የሚሻ ነው” ብለዋል። በመሆኑም በስልጠናው ችግሩን ለመከላከል ከእያንዳንዳችን ምን እንደሚጠበቅ እና ምን ማድረግ እንዳለብን እንድትመክሩ ሲሉ ም/ፕሬዚዳነቱ ለሰልጣኞች መልዕክት አስተላልፈዋል።

የስልጠና ፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ በለጠ መሀሪ “የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ምንነትን ያስረዱ ሲሆን ድህነት እና ስራ አጥነት፣ ህገወጥ ደላሎች መበራከት፣ የህብረተሰቡ የተሳሳተ ግንዛቤ እና የህገ-ወጥ ድርጊቱ ተዋናኞች ቁጥር መብዛት ዋና መንስኤዎች ናቸው በመሆኑም የባለድርሻ አካላትን ብሎም አጠቃላይ የማህበረሰባችን ግንዛቤ ማሳደግ ችግሩን ለመከላከል ቅድመ ሁኔታ በመሆኑ ይህን ስልጠና አዘጋጅተናል” ብለዋል።

በተመሳሳይ ዶ/ር የሺዋስ እባቡ እንዳሉት “ሀገራችን ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገሮች በተለየ በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጠቂ ስትሆን እኛ የምንገኝበት የሰሜን ምዕራብ አካባቢ በመተማ – በሱዳን፣ በሊቢያ በኩል ወደ ጣሊያን እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት የሚደረግ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ከምንጩ ለመቅረፍ ለአካባቢያችን ማህበረሰብ ይህን አይነት ስልጠና መስጠት አዎንታዊ አስተዋፅኦ ይኖረዋል” ብለዋል።

ስልጠናው ከገንደ ውሃ ከተማ፣ ከመተማ ወረዳ እና ከጎንደር ዙሪያ የተውጣጡ 48 የሀይማኖት አባቶች፣ የፍትህ አካላት እና በድርጊቱ ሰለባ የሆኑ ግለሰቦች (ከስደት ተመላሽ የሆኑ) እና ቤተሰቦቻቸው እየተሳተፉ ሲሆን ስልጠናው ነገም ይቀጥላል።



